ምርጫ ቦርድ በእስር ላይ የሚገኙትን እነ አቶ እስክንድር ነጋን በዕጩነት ሊመዘግብ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችን በምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ሊመዘግብ መሆኑን ፓርቲው ገልጸ።

በምርጫው በዕጩነት እንዲቀርቡ ተወሰነላቸው የተባሉት ግለሰቦች ክስ ተመስርቶባቸው አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ አመራሮች አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም እና አስካለ ደምሌ ናቸው።

በዚህም መሠረት ዛሬ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነበረው ችሎት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎቱ በእስር ላይ ያሉ የፓርቲው አመራሮች በዕጩነት እንዲመዘገቡ የሰጠውን ውሳኔ በመፈፀም ላይ እንደሆኑ መግለጻቸው ተነግሯል።

ዛሬ ግንቦት 26/2013 ዓ.ም ጉዳዩን በተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ላይ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ የባልደራስ ፓርቲ ለምርጫ እንዲቀርቡለት የሚፈልጋቸውን ዕጩዎች እንዲያሳውቅ ቦርዱ መጠየቁን አስፈላጊው ነገር እተከናወነ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት እነ አቶ እስክንድር ነጋ በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ያሳለፈውን ውሳኔ ለማስፈፀም እንደሚቸገር አስታውቆ እንደነበር ይታወሳል።

ሰብሳቢዋ ጨምረውም ቦርዱ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መስራች እና ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት የፓርቲው አባላትን በምርጫው እንዲሳተፉ ለማድረግ ቦርዱ 1.3 ሚሊዮን ወረቀት ማስወገዱንና በአምስት ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ ዕጩዎቹን ለማካተት እየሰራ መሆኑን መናገራቸውን ባልደራስ ገልጿል።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ የባልደራስ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ገለታው ዘለቀ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ፓርቲው የምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የታሰሩ አባላቱን ከግምት ውስጥ አስገብተው ቅስቀሳ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውሳኔ በኋላም ቅስቀሳውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

"ለእነ እስክንድር ስለተፈረደ ሳይሆን ለፍትህ ሲባል ወደ ታች ያሉ ዳኞችም እንደዚህ ቆራጥ ውሳኔ መስጠት አለባቸው፤ በውሳኔው እና ሂደቱ በዚህ በመዘጋቱ ደስተኞች ነን" ሲሉ አቶ ገለታው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባልደራስ ሊቀ መንበሩን አቶ አስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች አመራሮቹ በምርጫ ቦርድ በዕጩነት እንዲመዘገቡ መጠየቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ቦርዱም አመራሮቹ በሕግ ቁጥጥር ስር የሚገኙ በመሆናቸው በምርጫው በዕጩነት መመዝገብ እንደማይችሉ በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎት ነበር።

ይህንን ውሳኔ ያልተቀበለው ፓርቲው ጥያቄውን በተመለከተ በምርጫ ቦርድ ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ የነበረ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ የምርጫ ቦርድን ውሳኔን አጽንቶ ነበር።

ነገር ግን ባልደራስ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት በመውሰድ ባቀረበው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ የቀረቡ መከራከሪያዎችን ከመረመረ በኋላ በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል።

አቶ አስክንድር ነጋና ሌሎች የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በታዋቂው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ከተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተከታተሉ ይገኛሉ።