ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የጨቅላ ህፃናትን ሞት መቀነስ እንዳልተቻለ ተጠቆመ
በኢትዮጵያ የጨቅላ ህፃናት ሞት መጠን ከ 1 ሺህ በህይወት ከሚወለዱት መካከል 33ቱ እንደሚሞቱ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቋል።
ይህም አሃዝ ከአምስት አመት በፊት ከአንድ ሺህ ህፃናት 29 ሞት ከነበረው ጭማሬ ማሳየቱም ተገልጿል።
ለህፃናቱ ሞት ምክንያቶች ተብለው የተገለፁትም በዋነኝነት የጨቅላ ህፃናት መታፈን (Asphyxia)፣ ኢንፌክሸን እና ያለ ጊዜያቸው የሚወለዱ ህፃናት ናቸው ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የቅድመ ወሊድ ክትትል አለማድረግ ፣ በጤና ማዕከላት አለመውለድ ቢወለዱም በቂ እና ጥራት ያለው አገልግሎት አለማግኘት፣ ሌሎች ምክንያቶች እንደሆኑም ተገልጿል።
በባለፉት 10 አመታት የእናቶች ሞትን መቀነስ ቢቻልም የጨቅላ ህፃናት ሞት ግን መቀነስ ባለመቻሉ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻም ተገልጿል።
ተቋሙ ይህንን ያስታወቀው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጣው መግለጫ ሲሆን የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ ከሚያዝያ 28-29 2013 ዓ.ም በቀረበ ፖሊሲ ላይ በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
በዚህ መድረክ ላይም የፓርላማ አባላት፣ ጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም የምርመራ ትግበራ ዳይሬክቶሬት ተቀዳሚ ዳይሬክተር ወይዘሪት ፊርማዬ እንደገለፁት ውይይቱ በዋነኝነት የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረውን ሃገር አቀፍ እንቅስቃሴ በመረጃ መደገደፍና ብሔራዊ የጨቅላ ህፃናትና ልጆች ስትራቴጂ ግብአት እንዲሆን ማድረግ ነው ብለዋል።
የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ መፍትሄ ተብለው ከቀረቡ ኃሳቦችም መካከል የጤና አገልግሎትን ማጠናከር፣ ከቅድመ እርግዝና ጀምሮ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን የጤና አገልግሎትን ማሻሻልና በየደረጃው ለሚሰጠው አገልግሎት የጥራት ደረጃ ማስቀመጥ መሆናቸውም ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ከህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት እና መሰረተ ልማት ጋር የተገናኙ ችግሮችም ሊፈቱ ይገባል ተብሏል።