ከ6.7 ቢሊየን ብር በላይ የሆነ የህወሓት ሀብት መያዙን ዐቃቤ ሕግ ገለጸ

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ህወሓት ሊጠቅምበት ይችል የነበረን ከ6 ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ቡድኑ እንዳያገኝ ማድረጉን አስታወቀ።

ከስድስት ወር በፊት በህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በቡድኑ አማካይነት በተለያየ መልኩ ይንቀሳቀስ ነበረን ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ "ለወንጀል መፈጸሚያነት እንዳይውልና እንዳይሸሽ ለማድረግ መቻሉን ገልጿል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በህወሓት ቡድን ላይ ባለፉት ወራት በተደረገው የሀብት ክትትልና ምርመራ ከ6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጣጠር የቻለ ሲሆን፤ በተጨማሪም 97 ሚሊዮን 573 ሺህ ብር በላይ የሆነ ሀብት በሕግ አግባብ የውርስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከተዉ አካል ማቅረቡን ገልጿል።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ውስጥ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል የሆኑት አቶ ዓለምአንተ አግደው እንዳሉት ይህን ያህል መጠን ያለው ሀብት ሊገኝ የቻለው በቡድኑ ተቋማትና በአመራሮቹ ላይ በተደረገ ክትትል ነው።

"የህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከፈጸሙ ማግስት ጀምሮ ቡድኑ ሲቆጣጠራቸው በነበሩ፣ ገንዘብና ንብረታቸውን ለሕገ-ወጥ አላማው ሊጠቀምባቸው ይችላል ተብለው በተጠረጠሩ ድርጅቶች እንዲሁም በጦርነት በተሳተፉ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ በተደረገ የሀብት ክትትልና ምርመራ የተገኘ ነው" ብለዋል።

በዚህም መሠረት "ክህደት ፈጽመው ከህወሓት ጋር በመሰለፍ በጦርነት ከተሳተፉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች 45 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብና ሀብት የተገኘ ሲሆን፤ በገዙት ሼር ደግሞ ወደ 10 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል" ብለዋል ኃላፊው።

በዚህም በአጠቃላይ ከ54 ሚሊየን 237 ሺህ ብር በላይ የተገኘ ሲሆን በተጨማሪም ሌሎች በርካታ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲታገዱ መደረጋቸው ተገልጿል።

ህወሓት የኢንዶውመንት ተቋም ነው በሚለው ኤፈርት ስር ከሚተዳደሩና ተያያዥ ከሆኑ ድርጅቶችም ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ እንዲሁም ሼር የተገዛበት 420 ሚሊየን የሚደርስ የገንዘብ መጠን ሲገኝ በአጠቃላይ ከ4 ቢሊየን 205 ሚሊየን ብር በላይ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደታገደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አመልክቷል።

በተጨማሪም ግምታቸዉ ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ የሆኑ 179 የደረቅና የፈሳሽ ጭት ማመላለሻ ከባድ ተሽከርካሪዎችን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣትና የጋራ የሕግ ትብብር ጥያቄ ለጅቡቲ መንግሥት በማቅረብ ወደ አገር እንዲመለሱ መደረጉ ተገልጿል።

በዚህም የኤፈርት ተቋማት ገንዘብና ንብረት "ለተጨማሪ የወንጀል ተግባር መፈጸሚያነት እንዳይውል የመከላከል ሥራ መስራቱን" ዐቃቤ ሕግ አመልክቶ፤ እየተደረገ ያለው የወንጀልና የሀብት ምርመራው ተጠናቆ ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ አስኪሰጥ የኤፈርት ድርጅቶች በፍርድ ቤት በተሾሙ ገለልተኛ ባለአደራ ቦርድ ስር ሆነው ሕጋዊ ሥራዎችን ብቻ እንዲያከናውኑ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ተብሏል።

ከዚህ ባሻገርም ዐቃቤ ሕግ በተመሳሳይ "በህወሓት ቡድን ውስጥ በነበሩ አመራሮች ቀጥተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸው ነበሩ" በተባሉ ሦስት የሲቪል ማኅበራት ላይ በተደረገ ምርመራ ከ400 ሚሊየን ብር በላይ እና ሼር የተገዛበት ከ5 ሚሊየን ብር በላይ አግኝቶ በፍርድ ቤት እንዲታገድና ገለልተኛ አስተዳዳሪ ተሹሞ በማኅበራቱ ገንዘብ ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት አማካይነት በተደረገው የሀብት ምርመራ የህወሓት የሆነ ከ97 ሚሊዮን ብር በላይ አግኝቶ በፍርድ ቤት አሳግዶ እንደነበር ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ ቡድኑ ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ላይ መሳተፉን መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከምዝገባ የሰረዘው መሆኑን ተከትሎ፤ በሕግ በሚያዘው መሠረት ቡድኑ የነበረበት ዕዳውን ተሸፍኖ የተረፈው ገንዘብ ለሥነ ዜጋና ለመራጮች ትምህርት እንዲውል ለቦርዱ መተላለፉን አቶ ዓለምአንተ አግደው ገልጸዋል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ ወታደራዊ እርምጃ ወስዶ ቡድኑን ከሥልጣኑ ማስወገዱ ይታወሳል።

ከዚህም በኋላ የህወሓት ከፍተኛ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች ላይ የእስር መዘዣ ከመውጣቱም በተጨማሪ በቡድኑ ስር ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ በርካታ የንግድና የአገልግሎት ተቋማት ላይ እግድ ተጥሎባቸው ተጥሎባቸው እንደተነበር ይታወቃል።