ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ ፡ እነ አቶ ስብሐት ነጋ ፍርድ ቤት ቀረቡ
አቶ ስብሃት ነጋና አቶ አባይ ወልዱን ጨምሮ ክሳቸው በሁለት መዝገብ የተያዘ ከአስራ አምስት በላይ የህወሓት አባላት ትናንት ፍርድ ቤት ቀረቡ ።
አቶ ስብሃት ነጋና አቶ አባይ ወልዱን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ ከሰባት ቀናት በፊት በጠየቀው ቀጠሮ መሰረት የደረሰበትን የምርመራ ሂደት ለችሎቱ አብራርቷል።
ተጠርጣሪዎቹ በሃገር ክህደት ወንጀል፣ በክልሉ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በማድረስና፣ በመሳሪያ በታገዘ አመፅና ሁከት በማነሳሳት በሚሉ ወንጀሎች ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።
ፖሊስ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና የተጠርጣሪዎቹን የስልክ ልውውጥ በሚመለከት ለአስፈላጊው መስሪያ ቤት ደብዳቤ ፅፎ መረጃ እየጠበቀ እንደሆነና ከዚህም በተጨማሪ የሰነድና ሌሎች መረጃዎችን እየሰበሰበ እንደሆነ በችሎት ውሎ አስረድቷል።
በእነ አቶ ስብሐት ነጋ፣ አቶ አባይ ወልዱ እና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በተከፈተ ሦስት መዝገብ የተካተቱ 21 ተጠርጣሪዎች ናቸው ፍረድ ቤት የቀረቡት።
በፍርድ ቤቱ ከቀረቡት መካከል የህወሓት መስራች የሆኑት አቶ ስብሐት ነጋና ለስምንት አመታት ያህል ትግራይን ያስተዳደሩት የቀድሞ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ፣ የፌደራል የገንዘብ ምክትል ሚኒስትር በኋላ ደግሞ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ይገኙበታል።
ተጠርጣሪዎቹ እስካሁን ክስ ያልተመሰረተባቸው ሲሆን ፖሊስ ቀጣይ የምርመራ ስራዎች እንደሚቀር ለችሎቱ በመግለፅ 14 ተጨማሪ ቀናት ተጠይቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲሆን መርማሪ ፖሊስ በዛሬው ችሎት ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀን የፈቀደ ሲሆን በዚህም መሰረት ለየካቲት 5፣ 2013 ዓ. ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ አድርገው ነበር።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ሰዎች ብዛት 349 መሆናቸውን ገልጸው፤ ከነዚህ ውስጥ 96 የሚሆኑት የህወሓት ቁልፍ አመራሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ተፈላጊ ከሆኑት አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች መካከል 124 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም ገልጸዋል።
ለእስር ማዘዣው ዋነኛ ምክንያቶቹ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል በመፈፀም፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።
በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክህደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸው ከነበሩ ሌሎች የህወሓት አመራሮች መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣ በተለያዩ የሥልጣን ቦታ ላይ የነበሩት አቶ አባይ ጸሐዬ፣ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊቱ ከድተዋል የተባሉት ኮሎኔል ኪሮስ ሐጎስ በግጭቱ ወቅት እጅ አልሰጥም በማለታቸው መገደላቸው ተነግሯል።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው መቃቃርና አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።
የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ የህወሓት አመራሮች ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ከገለጹ በኋላ ስላሉበት ሁኔታና ወቅታዊ ጉዳዮች በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም። የህወሓት ፕሬዚዳንት የሆኑት ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) የት እንዳሉ አይታወቅም።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።
ነገር ግን አልፎ አልፎ ውጊያ እንደሚካሄድ የተነገረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ "የከፋ" ሲል ገልጾታል።