ወደ አገር ገቡ በተባሉት ገጀራዎች ላይ የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ እያደረኩ ነው አለ

ወደ አገር ውስጥ ገብተው በጉምሩክ አማካይነት ስለተያዙት ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ገጀራዎች በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ገጀራዎቹ የገቡበት ሰነድን ጨምሮ ለምን አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ ዝርዝር ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል።

ትናንት [ሰኞ] የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የገቢዎች ሚኒስቴርን ጠቅሰው በትልቅ ኮንቴይነር ተጭነው "በሕገ ወጥ ሰነድ ወደ አገር ውስጥ የገቡ ገጀራዎች መያዛቸውን" ተዘግቦ ነበር።

የገቢዎች ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ላይ ከምስል ጋር እንዳሰፈረው መነሻቸው ቻይና የሆኑትና ብዛታችው 186 ሺህ 240 የሆኑትን ገጀራዎችን ሞጆ ደረቅ ወደብ ከደረሱ በኋላ አስመጪው "ከፌዴራል ፖሊስ የተፈቀደለት በማስመሰል እና ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ለማሳለፍ ሞክሯል" ሲል አመልክቷል።

ሆኖም የቀረበው ሰነድ ሕጋዊነት ገና እየተጣራ ባለበት ሁኔታ እንዲህ አይነት ትክክል ያልሆነ መረጃ መውጣቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ገጀራዎቹ ተገቢውን ታክስ ከፍለው በሕጋዊ መንገድ ሞጆ መድረሳቸውን የገለጹት ኃላፊው ሞጆ ከደረሱ በኋላ አስመጪው እቃዎቹን ለመውስድ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም "በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ" ምክንያት ከፌዴራል ፖሊስ ማረጋገጫ እንዲያመጡ በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በዚህም "የምርጫ ጊዜ ስለሆነ ከፖሊስ ፍቃድ አምጡ ሲሏቸው የሆነ ወረቀት አጽፈው ይመጣሉ። ጉምሩክ ደግሞ ይሄ ነገር መጣራት አለበት ብሎ እሱ እየተጣራ ነው። ተጣርቶ ፎርጅድ [ሐሰተኛ ሰነድ] መሆኑ ከተረጋገጠ ሰዎቹ ተጠያቂ ይሆናሉ" ብለዋል አቶ ጄላን። አሁን ላይ ግን ምንም የተረጋገጠ ነገር አለመኖሩንም ጠቁመዋል።

አስመጪዎቹ ገጀራዎቹን ያስገቡበት ምክንያትም እየተጠራ ነው ያለው ያሉት ኃላፊው በእነርሱ በኩል ግን '"ለልማት" ሥራ እንደሆነ መግለጻቸውን ጠቁመዋል።

እናም ይህ ጉዳይ በምርመራ ሂደት ላይ እያለ መረጃው መሰራጨቱን አመልክተው ፖሊስ ግን ገጀራዎቹ የገቡበት ሰነድ ትክክለኛነትና ለምን ጉዳይ ወደአገር ውስጥ እንደገባ ምርመራ እኣደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በምርጫና በአገራዊ የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት ከሳምንታት በፊት የግብርና ሚኒስቴር ከውጪ አገር ያስገባቸው ገጀራዎች እንዳይሰራጩ እገዳ መጣሉንም አቶ ጄይላን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የገቢዎች ሚንስቴር በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ የነበረ 186 ሺህ በላይ ገጀራ መያዙን እና የዕቃው ባለቤት እና አስተላላፊው /ትራንዚተሩ/ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ በይፋዊ ፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ከ15 ቀን በፊት በአንድ አስመጪ ብዛቱ 186,240 የሆነ ገጀራ በአራት ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮች ከቻይና ተጭኖ ሞጆ ጉምሩክ ተጓጉዞ መድረሱን አመልክቷል።

ዕቃው በዲክላራሲዮን ቁጥር 4-1919/21 ተመዝግቦ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ የተፈቀደለት በማስመሰል እና ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ ለገቢ ዕቃ አወጣጥ የሰነድ መርማሪው አቅርቦ ሰነዱ ተመርምሮ ከ7.7ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት ተለቆ እንደነበር አስታውቋል።

ገጀራው ከተለቀቀ በኋላ በጉምሩክ ኮሚሽን እና በሞጆ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኢንተለጀንስ በኩል ክትትል ተደርጎ የቀረበው ሰነድ ሲጣራ ሐሰተኛ እና ዕቃውም ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑ መረጋገጡንም ጠቁሟል።

ይህ ጉዳዩ ከ15 ቀን በፊት የተከሰተ ቢሆንም፤ አስመጪው ያቀረብኩት ሰነድ ሕጋዊ ነው በማለት ቅሬታ ስላቀረበ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጋር በጋራ ሲጣራ ቆይቶ ሰነዱ ሐሰተኛ እና ከፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው መሆኑ መረጋገጡን ሚኒስቴሩ አመልክቷል።