ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እንዲጠራ ሃሳብ አቀረበች
በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደውን ድርድር ለማስቀጠል ሊደረግ የሚገባው የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የመሪዎች ስብሰባ እንዲጠሩ መጠየቅ መሆኑን ኢትዮጵያ አስታወቀች።
ይህ የተገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሱዳኑ አቻቸው ለጻፉት ደብዳቤ በሰጡትም ምላሽ ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።
በዚህም በቀጣይነት የሚደረገውን ድርድር ለማካሄድ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የዲሞክራቲክ ኮንጎው ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ የሕብረቱን የመሪዎች ጉባኤ እንዲጠሩ መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የርዕሰ ብሔራን እና መንግሥታት ጉባኤ የአፍሪካ ሕብረት የመጨረሻው የስልጣን እርከን ነው።
የመሪዎች ጉባኤው የአፍሪካ ሕብረት ፖሊሲዎችን ያጸድቃል፣ የሕብረቱን ቀዳሚ አጀንዳዎች ይለያል፣ ዓመታዊ እቅዶችን ያወጣል እንዲሁም አፈጻጸሞችን ይከታተላል።
ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበርን ይመርጣል፣ አዲስ አባል አገራትን ወደ ሕብረቱ ያስገባል፣ በአፍሪካ ሕብረት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ይሰጣል።
ይህ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በዓመት አንድ ጊዜ በሐምሌ/ነሐሴ ወር ላይ የሚካሄድ ሲሆን አንድ የሕብረቱ አባል ጥያቄ ከቀረበ እና ጥያቄው በሁለት ሦስተኛ አባል አገራት የሚጸድቅ ከሆነ ግን ጉባኤው አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከአንድ ሳምንት በፊት ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ለደረሳቸው ደብዳቤ ምላሽ በሰጡበት ደብዳቤ ላይ፤ በግድቡ ዙሪያ የተካሄደው ውይይት እንዳልተሳካ መቁጠር አግባብ አይደለም ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም የመርሆዎች ስምምነት መፈረም እና የብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንስ ምርምር ቡድን መመስረቱ የድርድሩ ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ በቅርቡ ተካሂዶ ከመግባባት ላይ ሳይደረስበት ስለቀረው ድርድርም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚካሄደው የሦስትዮሹ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት መሪነት እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎትት እንዳላት በደብዳቤያቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በስምምነቱ መሠረት የአውሮፓ ሕብረት፣ ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ በተደረሰው ስምምነት መሠረት በታዛቢነታቸው እንዲቀጥሉ እና የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የአስተባባሪነት ኃላፊነታቸውን መወጣት አስፈላጊነትን አንጸባርቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሕጋዊ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች እንዳይሳኩ እንቅፋት መሆናቸውን፤ "ሁሉም አካላት በቀና መንፈስ ወደ ድርድሩ ቢገቡ ሁሉንም ተጠቃሚ ከሚያደርግ ስምምነት መድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል።
በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስካሁን ሲጓተት ቆይቶ በግንባታ ላይ አስር ዓመትን አስቆጥሯል።
ተገንብቶ ሲያበቃ በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን የተነገረው ግድቡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግንባታ ሥራው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የተነገረለት ይህ ግድብ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ፣ ለኢንዱስትሪዎችና ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።