ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሶልሻዬር፡ "ይህን ያደረገው ልጄ ቢሆን ኖሮ ምግብ አልሰጠውም ነበር"
የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኦሌ ጉናር ሶልሻየር ቡድኑ በአጨቃጫቂ ሁኔታ ቶተንሃም ሆትስፐርን 3-1 ከረታ በኋላ "የጨዋታ ውበት ጠፍቷል" ሲሉ ተደምጠዋል።
የዩናይትዱ ኤዲሰን ካቫኒ ያስቆጠረው ጎል ዳኛው ጎሉ ከመግባቱ በፊት ጥፋት ተፈፅሟል ብለው የቪድዮ ማስረጃውን ካዩ በኋላ እንዲሻር ወስነዋል።
የቶተንሃሙ ሶን የዩናይትዱ ስኮት ማክቶሚናይ በጣቱ ፊቴን ጭሮኛል ብሎ መሬት ላይ ወድቆ ሳለ ነው ጎሉ የተቆጠረው።
"ልጄ ይሄን ቢያደርግና የቡድኑ አጋሮቼ መጥታችሁ ካላነሳችሁ ቢል ምግብ ነበር የምቀጣው፤ ምክንያቱም ይህ አሳፋሪ ድርጊት ነው" ሲሉ ሶልሻዬር በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ምሬታቸውን ገልፀዋል።
"ጨዋታው ውበቱ ጨርሶ እየጠፋ ነው።"
የቶተንሃሙ ሶን ከአጨቃጫቂው ክስተት በኋላ ዩናይትድ ላይ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ 1-0 ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ፍሬድ፣ ካቫኒ እንዲሁም ግሪንውድ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ዩናይትድ 3-1 ረትቷል።
ሶልሻዬር ሶን ላይ የተፈፀመው ጥፋት ግልፅ ቢሆን ኖሮ ዳኛው ቢመለከተው አይገርመኝም፤ ጎሉ ግን መፅደቅ ነበረበት ብለዋል።
"እኛ በሶን አላታለልንም። ዳኛው ግን ተሸውደዋል።"
የቶተንሃሙ ጆዜ ሞውሪንሆ በበኩላቸው "በመጀመሪያ አንድ ነገር ልንገራችሁ። ሶልሻዬር ስለ ሶኒ ያንን አስተያየት ከሰጠ በኋላ እኔን አለመጠየቃችሁ ገርሞኛል" ብለዋል።
"እኔ ብሆን ኖሮ አንድ ተጨዋች ይህንን አድርጓልና እራት አልሰጠውም ያልኩት ምን ሊፈጠር ይችል ነበር? እጅግ በጣም ነው የሚያሳዝነው። ሌሎችን በምታዩበት ዓይን እኔን አለማየታችሁ እጅግ ያሳዝናል።"
"ስለ ሶን ከጠየቃችሁኝ ኦሌ አባቱ አለመሆኑ ዕድለኛ ነው። እኔ አባት ነኝ። አባት ሁሌም ልጁን ሊመግብ ይገባል። ለልጅህ መስረቅ ካለብህ ትሰርቃለህ" ብለዋል ጆዜ።
የቶተንሃሙ ሶን ሄውንግ-ሚን በስኮት ማክቶሚናይ ከተነካ በኋላ ለደቂቃዎች መሬት ላይ ወድቆ ቆይቷል።
የስፐርሱ ጆዜ ሞውሪንሆ የቪድዮ እገዛ [ቪኤአር] ቀንደኛ ተቃዋሚ ናቸው።
"ለሁሉም ከባድ ነው። ለኛ፣ ለተጨዋቾች፣ ለዳኞች። በርካታ የሚጋጩና የማይገቡ ውሳኔዎች እየተስተዋሉ ነው። ይህ የኔ ችግር አይደለም። ላስተካክለው አልችልም።"
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች በአጨቃጫቂ የቪኤአር ውሳኔዎች የታጀቡ ሆነዋል።
አርብ ምሽት ዎልቭስ ፉልሃምን ሲያሸንፍ ፉልሃሞች ያስቆጠሩት ጎል ከጨዋታ ውጭ ተብሎ መሰረዙ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።
ቅዳሜ ከሰዓት ደግሞ ሊቨርፑል አስተን ቪላን ባሸነፈበት ጨዋታ አንድ ጎል ከጨዋታ ውጭ ተብሏል።
ሞውሪንሆን የፉልሃምን ጨዋታ ስመለከት ነበር ብለዋል። "እኔም ምንም እየገባኝ አይደለም። አንዳንዴ ታገኛለህ። አንዳንዴ አታገኝም። ጎል አስቆጥረህ ለመደሰት ትፈራለህ።"
ሞውሪንሆ ከዩናይትድ ጋር በነበረው ጨዋታ ስፐርስ ሊሸነፍ አይገባውም ነበር ሲሉ ተደምጠዋል።
በሌላ በኩል የእግር ኳስ ተንታኞች ስለ አጨቃጫቂው ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ ተጨዋች ሮይ ኪን ስካይ ስፖርት ላይ በሰጠው አስተያየት "ይሄ ጥፋት ከሆነ ወደ ቤታችን ብንሄድ ነው የሚሻለው" ብሏል።
የቀድሞ አየርላንዳዊው አጥቂ ክሊንተን ሞሪሰን ቢቢሲ ራድዮ 5 ላይ በሰጠው አስተያየት "ይሄ በፍፁም ጥፋት ሊሆን አይችልም" ሲል የሶንን ድርጊት አጣጥሏል።
ተንታኙ እንደሚለው ዳኛው ይሄ ጥፋት ነው ብለው ካመኑ ቀድሞ አንድ ቢጫ ላየው ስኮት ማክቶሚናይ ሁለተኛ ቢጫ አሳይው ከሜዳ ሊያሰናብቱት ይገባ ነበር።
"ጨዋታው ቅጥ እያጣ ነው። ተመሳሳይ ውሳኔዎች አይስተዋሉም" ብሏል ተንታኙ።