ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኢል ኦማር ጊሌ ለ5ኛ ጊዜ ምርጫ አሸነፉ
የጂቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ለ5ኛ ጊዜ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ከመራጩ ሕዝብ 98 ከመቶ ድምጽ በማግኘት አሸነፉ።
ብቸኛው ተፎካካሪያቸው የነበሩት ዛካሪያ ኢስማኢል ፋራህ 1.59 በመቶ ብቻ የመራጮችን ድምጽ ሊያገኙ መቻላቸው ተነግሯል።
የዋነኛው ተቃዋሚ መሪው ዕጩ ባለፈው አርብ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድኔ በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ እንግልት ደርሶበታል በሚል ድምጽ ሳይሰጡ ራሳቸው ከውድድሩ አግልለው ነበር።
ምርጫውን በበላይነት የመሩት የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ ሙሚን አሕመድ ሼክ አርብ ዕለት 177 ሺህ መራጮች ድምጽ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ላይ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡት ሰዎች ድምር 200 ሺህ እንደነበር ተዘግቧል።
ኤስማኤል ጊሌ አሁን የ73 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ እንደ አውሮፓውያን ከ1999 ጀምሮ በጂቡቲ የፕሬዝዳንተንት የሥልጣን መንበር ላይ ቆይተዋል።
የዘንድሮውን ምርጫም በከፍተኛ የበላይነት በማሸነፋቸው ለሚቀጥሉት 5 ዓመታት ጂቡቲን እንዲመሩ ያስችላቸዋል ተብሏል።
በቆዳ ስፋት አነስተኛ ሆና ነገር ግን በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ አካባቢያዊና ወታደራዊ ቦታ የያዘችው ጂቡቲ ጠቅላላ የሕዝብ ብዛቷ ከአንድ ሚሊዮን ያነሰ ነው።
አሜሪካ፣ ቻይናና ፈረንሳይ በጂቡቲ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ገንብተዋል።
የዓለም ባንክ በቅርብ ያወጣው አንድ መረጃ ከ14 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ጂቡቲያዊያን በከፍተኛ የድህነት ውስጥ ነው የሚኖሩት ይላል።