ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግብጽ የ3ሺህ ዓመት ዕድሜን ያስቆጠረ አስደናቂ ጥንታዊ ከተማ ተገኘ
ግብጽ አሸዋ ቀብሮት የነበረና 3ሺህ ዓመታት ዘመንን ያስቆጠረ ግዙፍ ጥንታዊ ከተማን በቁፋሮ አገኘች።
ይህ የቁፋሮ ግኝት ከፈርኦን ቱቱካሙን መቃብር ቀጥሎ እጅግ አስደናቂ የቁፋሮ ውጤት ተብሎ ተሞካሽቷል።
ዕውቁ ኢጂብቶሎጂስቱ (የግብጽ ጥንታዊ ታሪክ አጥኚ) ዛሒ ሐዋስ የዚህን ወርቃማ ጥንታዊ ከተማ ግኝትን ሐሙስ ዕለት ለዓለም አብስረዋል።
ዛሒ ሐዋስ እንዳሉት ከሆነ በግብጽ ታሪክ ይህ ጥንታዊ ከተማ እስከዛሬ ከተገኙ ጥንታዊ ከተሞች ሁሉ በግዝፈቱም ሆነ በያዘው አንጡራ ቅርስም ቢሆን የሚስተካከለው የለም።
የዚህ ከተማ ግኝት እውን የሆነው ሳምንታትን ብቻ በፈጀ ቁፋሮ ሲሆን አሸዋ መማስ የተጀመረው ገና በመስከረም ወር ላይ ነበር።
ይህ ግዙፍ ጥንታዊ ከተማ በታሪክ ውስጥ የሚታወቀው በፈርኦን አሜንሆቴፕ ሣልሣዊ ዘመነ መንግሥት ነበር።
ይህ ንጉሥ ጥንታዊት ግብጽን የገዛው ከ1391 እስከ 1353 ዓመተ ዓለም (ከክርስቶስ ልደት በፊት) ነበር።
ይህ አሁን የተገኘው ከተማ ስሙ አቴን ይባል ነበር።
ከፈርኦን ንጉሥ አሜንሆቴፕ ሣልሣዊ ሌላ ቀዳማዊ ፈርኦን እና ዝነኛውና ትንሹ ፈርኦን ቱቱንካሙን ይህን ከተማ መናገሻቸው አድርገውት በታሪክ ተዘግቦ ይገኛል።
የእነዚህ ሁለት ፈርኦኖች መቃብር ለሺህ ዘመናት በመልካም ይዞታ ላይ እንደኖረ በ1922 በእንግሊዛዊው ዕውቅ የአርኪዮሎጂ ጥናት ባለሙያ ሃዋርድ ካርተር መገኘቱ ይታወሳል።
የኢጂፕቶሎጂ ፕሮፌሰርና የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ቤሲ ብራያን የዚህን ጥንታዊ ከተማ መገኘት ከፈርኦን ቱቱንካምን መቃብር መገኘት ቀጥሎ ለዓለም የተበሰረ እጅግ ወሳኙ ግኝት ሲሉ አሞካሽተውታል።
ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት የዚህ ጥንታዊ ከተማ መገኘት በጥንታዊ ግብጻውያን አኗኗር ዙሪያ ብዙ የሚነግረን ነገር ይኖራል።
ይህ ጥንታዊ ከተማ መገኘቱን ተከትሎ በርካታ ጠቃሚ ነገሮችም በግኝቱ ተካተዋል። ከእነዚህ መካከልም ውድ ጌጣጌጦች፣ በቀለም ያጌጡ የእንስራና ሌሎች የፈርኦኑ ምልክት ያለባቸው የዕደ ጥበብ ውጤቶች ይገኙበታል።
ይህ የቁፋሮ ቡድን የዚህን ከተማ ፍለጋ የጀመረው ከካይሮ በስተደቡብ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቫሊ ኦፍ ኪንግስ ምዕራብ ሉክዘር አካባቢ ነበር።
"ቁፋሮው በተጀመረ በሳምንታት ውስጥ ሁሉንም የከርሰ ምድር ጥናት ተመራማሪዎችን ራሳቸውን ጉድ ባሰኘ ሁኔታ የሸክላ ድርድሮች መታየት ጀመሩ፤ ይህም የጥንታዊ ከተማውን አቅጣጫ መራን" ብለዋል ታዋቂው ኢጂፕቶሎጂስቱ ዶ/ር ሐዋስ።
የግኝቱ ሌላው አስደናቂ መልክ ደግሞ የጥንታዊ ከተማው አስደናቂ ግንቦችና አንዳንድ የመኖርያ መንደሮች እንዲሁም ቤቶችም ከዕለታዊ ቁሳቁሶቻቸው ጭምር መገኘታቸው ነው።
7ኛ ወሩን ባስቆጠረው የቁፋሮ ፍለጋ ከተገኙት አስደናቂ ነገሮች መሀል የከተማዋ አስተዳደር፣ የመኖርያ ሰፈሮች እና ዳቦ ቤት ይገኝበታል ተብሏል።
ከዚህ ቀደም በርካታ የውጭ አገር ተመራማሪዎች ይህን ጥንታዊ ከተማ ለማግኘት ብዙ ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቶ ነበር።
አሁንም በዚህ ጥንታዊ ከተማ ሌሎች ቁሳቁሶችን ፍለጋ የቀጠለ ሲሆን ተስፋ የተጣለው የፈርኦን ዕውቅ ነገሥታት መቃብርና ውድ ሀብቶቻቸው የተቀበሩበትን ቦታ ፈልጎ ማግኘት ነው።
ግብጽ ከከሸፈው የፀደይ አብዮት ወዲህ ተዳክሞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ማነቃቃት ከፍተኛ ፍላጎት አላት። ይህ ግኝት በዚህ ረገድ ትልቅ ውጤት ያስገኝላታል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት ግብጽ የጥንታዊ መሪዎቿን መቃብርና በመሚ ዘዴ የደረቁ የፈርኦኖችን አስከሬን ወደ ካይሮ ማዘዋወሯ ይታወሳል።
ይህ ሂደት 18 እጅግ ጥንታዊ ንጉሦችንና 4 ንግሥቶችን ያካተተ ነበር። እስከዛሬ ከቆዩበት የግብጽ ሙዚየም ወደ አዲሱ ብሔራዊ ሙዝየም ነው የተወሰዱት።
ይህ አዲስ ብሔራዊ ሙዝየም 1 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የወጣበት እጅግ ዘመናዊ መካነ ቅርስ ነው።
ከእነዚህ ወደ አዲሱ መካነ ቅርስ ከተዛወሩት የፈርኦን አስከሬኖች መካከል የአሜንሆቴፕ ሣልሣዊና ባለቤቱ ንግሥት ቲዬ አስከሬኖች ይገኙበታል።