ኢራን በኒውክሌር ተቋሟ ላይ 'እስራኤል ፈጸመች' ያለችውን ጥቃት እንደምትበቀል ዛተች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኢራን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል በአገራቸው የኒውክሌር ማዕከል ላይ ለፈፀመችው ጥቃት "የበቀል እርምጃ" እንወስዳለን ሲሉ ዛቱ።
የኢራን ባለሥልጣናት ናታንዝ የዩራኒየም ማበልፀጊያ እሁድ ዕለት መጀመሪያ የኃይል መቋረጥ አጋጥሞት ነበር ቢባልም በኋላ ግን "በኒውክሌር አሸባሪዎች" ጥቃት ደርሶበት ነበር ብለዋል።
ለዚህ ጥቃትም ባለሥልታነቱ ዋነኛ ጠላታችን የሚሏትን እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል።
አዲስ የተገነባው የዩራኒየም ማበልጸጊያ ጥቃቱ ሲገጥመው ገና ሥራ መጀመሩ ነው።
እስራኤል በጉዳዩ ላይ አስተያየቷን ባትሰጥም የአገሪቱ የሕዝብ ሬዲዮ የደኅንነት ምንጮችን በመጥቀስ የተፈጸመው ጥቃት በአገሪቱ የስለላ ተቋም ሞሳድ አማካይነት በመረጃ መረብ ላይ የተካሄደ ተልዕኮ ነው ብሏል።
እንደ ሬዲዮው ከሆነ ኢራን ከገለፀችው በላይ የከፋ ጉዳት ማብላያው ላይ ደርሷል።
የአሜሪካ የደኅንነት ባለሥልጣናት ለኒውዮርክ ታይምስ እንደነገሩት ከሆነ ከፍተኛ ፍንዳታ ከመሬት በታች ለሚገኘው ማዕከል ኃይል የሚያቀርበውን ውስጠኛ ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ አውድሞታል።
በስፍራው ማብላያውን ዳግም ወደ ሥራ ለማስገባት ዘጠኝ ወራት ያስፈልጋሉም ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ኢራን እኤአ በ2015 ከቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ጋር የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመገደብ እና አሜሪካ የጣለችባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ስምምነት አድርጋ ነበር።
ነገር ግን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ አሜሪካ ከዚህ ስምምነት ወጥታ ቆይታለች።
አዲሱ የጆ ባይደን መንግሥት ወደዚህ ስምምነት ለመመለስ እንደሚፈልግ ተገልጿል።
እስራኤል ግን ስለ ኢራን ስለምታካሂደው የኒውክሌር ፕሮግራም ማስጠንቀቂያዎችን ስትሰጥ ቆይታለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደረሰው ምን ነበር?
ኢራን ውስጥ አዲስ የዩራኒየም ማብላያ መሳሪያ ይፋ በተደረገ ማግሥት የኒውክለር ተቋሟ "አሻጥር" እንደተሰራበት አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ የኒውክሌር ባለሥልጣን ነበር የተናገሩት።
ይህ የሆነው እሁድ ዕለት ሲሆን በአገሪቱ ዋና ከተማ ቴህራን ደቡባዊ ክፍል የሚገኘው ናታንዝ በተሰኘው ተቋም ላይ የኤሌትሪክ ኃይል መቋረጥ አጋጥሞ ነበር ተብሏል።
የኢራን አቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ከፍተኛ ኃላፊ አሊ አክባር ሳሌሂ ይህንን የኤሌትሪክ ኃይል እንዲቋረጥ ያደረገው "የሽብር ተግባር" ያሉትን ማን እንደፈፀመው ይፋ አላደረጉም።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ግን የደኅንነት ምንጮችን ጠቅሰው እስራኤል ባደረሰችው የሳይበር ጥቃት የተከሰተ ነው ሲሉ ዘግበዋል።
እስራኤል ስለክስተቱ በይፋ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥባለች።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢራን ስለምታካሂደው የኒውክሌር ፕሮግራም ማስጠንቀቂያ ስትሰጥ እንደነበር ይታወሳል።
ይህ ክስተት የተፈጠረው በ2015 ተገብቶ የነበረውን የኒውክሌር ስምምነት በ2018 በትራምፕ አስተዳደር ከተገፋ በኋላ ዳግም ለማስቀጠል በሚታሰብበት ወቅት ነው።
ቅዳሜ ዕለት የኢራን ፕሬዝዳንት ሀሰን ሩሃኒ በናታንዝ አዲስ ማብላያ ሲመረቅ ተገኝተው ነበር።
ማብላያው የበለፀገ ዩራኒየም ለማምረት የሚረዳ ሲሆን ይህም ለነዳጅ ምርት ካልሆነም ደግሞ የኒውክሌር መሳሪያ ለማምረት ያገለግላል።
ይህ የኢራን ድርጊት አገሪቱ በ2015 የገባችውን ስምምነት የሚጥስ ሲሆን በወቅቱ የተወሰነ መጠን ያለው የበለፀገ ዩራኒየም ለማምረትና እና ለማከማቸት ብቻ ስምምነት ላይ ደርሳ ነበር።
ይህ የምታመርተው ዩራኒየምም ለተወሰኑ የኃይል ማምረቻዎች እንደ ነዳጅ በመሆን እንዲያገለግል ታቅዶ ነበር።
እሁድ ዕለት የኢራን አቶሚክ ኢነርጂ ድርጅት ቃል አቀባይ ቤህሮዝ ካማልቫንዲ እንዳሉት "ክስተቱ" ያጋጠመው ጠዋት በኒውክሌር ማምረቻው የኃይል ኔትወርክ ላይ ነው።
ካልቫንዲ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን ነገር ግን ለኢራን ፋርስ የዜና ኤጀንሲ "ምንም አይነት አደጋ ወይንም ያመለጠ ነገር የለም" ሲሉ ተናግረዋል።
በኋላም ላይ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ከመስሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ አሊ አክባር ሳሌሂ የተሰጠ መግለጫ ያቀረበ ሲሆን ድርጊቱን "አሻጥር" እና "የኒውክሌር ሽብርተኝነት" ሲል ገልፀውታል።
በመግለጫው ላይ አክለውም "ይህንን አሳፋሪ ተግባር እያወገዝን እስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከኒውክሌር ሽብርተኝነት ጋር እንዲያዩት እንደምትፈልግ እንጠይቃለን" ብለዋል።
የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ክስተቱ ስለመፈጠሩ መረጃ እንደደረሰው ገልጾ፣ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
ባለፈው ሐምሌ ወር በናታንዝ በሚገኘው ተቋም ላይ በተከሰተ እሳት የማዕከላዊ ማብላያውን መገጣጠሚያ ወርክሾፕ ያቃጠለ ሲሆን የአደጋው መንስኤ አሻጥር መሆኑ ተገልጾ ነበር።
እኤአ በ2015 ኢራን እና ስድስት አገራት ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ሲሆን በዚህ ስምምነት ላይም ኢራን የተወሰኑ የኒውክሌር ተግባራቷን ለማቋረጥ ስትስማማ በምላሹም ምጣኔ ኃብቷን እየጎዳው ከሚገኘው የተጣለባት ቅጣት ወይንም ማዕቀብ እንደሚላላ አልያም እንደሚነሳ ተቀምጧል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኀን፣ ካን ስሙን ያልገለፀው አንድ የደህንነት ምንጭ ጠቅሶ በተቋሙ ላይ ያጋጠመው የኃይል መቋረጥ የእስራኤል ሳይበር ኦፕሬሽን በወሰደው እርምጃ ነው ብሏል።
ሮን ቤን ዪሻሂ የተሰኙ የመከላከያ ተንታኝ ለ ዋይኔት የዜና ድረገጽ እንዳሉት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመታጠቅ እያደረገች ያው ግስጋሴ ስጋት ነው ብሎ ለማሰብ በቂ ነው ካሉ በኋላ፣ የኃይል መቋረጡ በአደጋ የተፈጠረ ላይሆን ይችላል ብለዋል።
አክለውም " . . .የኒውክሌር ሩጫ ግስጋሴን ለማስቆም ከአሜሪካ ጋር በተደረገ ስምምነት ይኹነኝ ተብሎ በተሰራ አሻጥር " ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ኢራን ከስድስቱ አገራት ጋር የገባችው ስምምነት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከስምምነቱ መውጣቷን ካስታወቁ በኋላ ውጥረት አስከትሏል።
አዲሱ የባይደን አስተዳደር ዳግም ስምምነቱን ለመመለስ የሚያስችል ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ጀምሯል።
ነገር ግን የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ባለፈው ሳምነት ስምምነቱ ዳግም ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት አስመልክተው ያስጠነቀቁ ሲሆን አገራቸው ከቴህራን ጋር በአዲስ ስምምነት እንደማትፈራረም አስታውቀዋል።












