የኤደንብራው መስፍን፣ ልዑል ፊሊፕ ለምን ንጉሥ አልተባሉም?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ልዑል ፊሊፕ የኤደንብራ መስፍን ነበሩ። ምናልባትም በዓለም ዝነኛው ባል ሊባሉ ይችሉ ይሆናል። ዘመናቸውን በሙሉ ቆፍጣና፣ ስፖርተኛና ሠርተው የማይደክማቸው ባተሌ ነበሩ።
የ780 ድርጅቶች ፕሬዝዳንት፣ አባልና የበላይ ጠባቂ ሆነው እድሜያቸውን አሳልፈዋል። በ143 አገራት ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል። ፈረንሳይኛና ጀርመንኛን አቀላጥፈው ይናገሩ ስለነበር የቋንቋ ችሎታቸው በብዙ መልኩ ረድቷቸዋል።
በተወለዱ በ99 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከግርማዊነታቸው ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ጋር ላለፉት ሰባት አስርታት አብረው በትዳር ዘልቀዋል። 73 ዓመት በትዳር መዝለቅ ቀላል ጊዜ አይደለም።
ፊሊፕ ለምን ንጉሥ አልተባሉም?
ለመሆኑ ንግሥቲቱን ካገቡ በኋላ የኤደንብራው መስፍን፣ ልዑል ፊሊፕን ለምን 'ንጉሥ ፍሊፕ' ሳይባሉ ቀሩ?
በቅድሚያ በንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ እነማን እንዳሉ እንዘርዝርና ለዚህ ጥያቄ ምላሽ እናገኛለን።
ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት እንደ አውሮፓውያኑ ከ1952 ጀምሮ የታላቋ ብሪታኒያ ርዕሰ ብሔር ናቸው። ይህም ማለት የንግሥቲቱ አባት ንጉሥ ጆርጅ 4ኛ ከሞቱ ዕለት ጀምሮ ማለት ነው።
ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት ርዕሰ ብሔር የሆኑት ለታላቋ ብሪታኒያ ብቻ አይደለም። ለሌሎች 15 አገራት ጭምር እንጂ።
በታላቋ ብሪታኒያ ታሪክ እንደ ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤት ንግሥናውን ለረዥም ጊዜ አጽንቶ የቆየ የለም።
ሌሎች የንጉሣዊያን ቤተሰቦችን ለመጥቀስ ያህል፡
1. የዌልሱ ልዑል ቻርለስ፣ ዕድሜ 72፣ ባለቤታቸው የኮርንዌሏ ካሚላ፣ ልዑል ቻርለስ የንግሥቲቱ የበኩር ልጅ ናቸው፡፡ ንግሥቲቱ ሲሞቱ ንጉሥ የሚሆኑትም እሳቸው ናቸው።
2. የኬምብሪጁ መስፍን፣ ልዑል ዊሊያም። ልዑል ዊሊያም የኬምብሪጇን ካትሪንን ነው ያገባው። ልዑል ዊሊያም የዌልሷ ልዕልት ዳያና የበኩር ልጅ ነው።
3. የሰሴክሱ መስፍን፣ ልዑል ሐሪ፡፡ ሐሪ የዊሊያም ወንድም ነው። ሐሪ ያገባው የሰሴክሷን ሜጋንን ሲሆን ባለፈው ዓመት ከንጉሣዊ ቤተሰብ ወጥተው በራሳቸው ሕይወትን ለመምራት መወሰናቸውን ይፋ አድርገው ነበር። አሁን የሚኖሩትም አሜሪካ ሎስ አንጀለስ ውስጥ ነው።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
እንዴት ነው የንጉሣዊ ቤተሰብ የሚኮነው?
አንድ ሰው የንጉሣዊ ቤተሰብ አባልን ሲያገባ/ስታገባ የንጉሣዊውን ቤተሰብ ይቀላቀላሉ። ትዳር ሲመሰርቱም የክብር ስም ይሰጣቸዋል።
ለምሳሌ ሌዲ ዲያና ስፔንሰር የዌልስ ልዕልት የተባለችው ከልዑል ቻርለስ ጋር በትዳር ስትጣመር ነበር። ይህም እንደ አውሮፓውያኑ በ1981 ዓ.ም የሆነ ነው።
ነገር ግን ንጉሥ ወይም ንግሥት ለመሆን ከንጉሣውያኑ ቤተሰብ ጋር በጋብቻ በመጣመር ብቻ የሚሆን አይደለም። የግድ ከንጉሣዊያን ቤተሰብ መወለድ ያስፈልጋል።
ይህም በመሆኑ አሁን በአልጋ ወራሽነት ቅደም ተከተል ለንግሥናው ከልዑል ቻርለስ የቀረበ ሰው የለም።

ከልዑል ቻርለስ ቀጥሎ ለዙፋኑ የቀረበው ሰው የልዑል ቻርለስ የመጀመሪያ ወንድ ልጅ ልዑል ዊሊያም ነው። ከልዑል ዊሊያም ቀጥሎ ደግሞ የልዑል ዊሊያም የበኩር ልጅ ልዑል ጆርጅ በ3ኛ ደረጃ ለዙፋኑ ይቀርባል።
ሟቹ ልዑል ፊሊፕ ግን መቼም ለዙፋኑ ቀርበው አያውቁም። ቅርብ ቢሆኑም ሩቅ ነበሩ።
ይህ ለምን ሆነ ብለን ስንጠይቅ በታላቋ ብሪታኒያ ንጉሥ ያገባች ሴት ንግሥት የሚለውን ስም ስትወስድ በተቃራኒው ግን ስለማይሰራ ነው። ይህም ማለት ወንድ ንግሥቲቱን ስላገባ የንጉሥነት ማዕረግን አያገኝም።
ልዑል ፊሊፕ ንጉሥ ሳይባሉ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትም ለዚሁ ነው።
ሆኖም ዳግማዊት ንግሥት ኤልዛቤት እና ልዑል ፊሊፕ አራት ልጆቻቸው ለዙፋኑ ቅርቦቹ ናቸው። አራት ልጆችንም አፍርተዋል።
ልዑል ቻርለስ የበኩር ልጅ ሲሆን አሁን ዕድሜው 72 ደርሷል። ልዕልት አን 70፣ ልዑል አንድሩ 61 እና ልዑል ኤድዋርድ 57 ዓመታቸው ነው።
የተነሳንበትን ጥያቄ መልሰናል። ስለዚህም ሟቹ የኤደንብራው መስፍን፣ ልዑል ፊሊፕ ንግሥቲቱን ስላገቡ ብቻ ንጉሥ ሊባሉ አልቻሉም።

የንጉሣዊያኑ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ምን ይመስላል?
የንጉሣዊ ቤተሰብ ጋብቻ ብዙውን ጊዜ የዓለምን ትኩረት የሚይዝ ነው። እጅግ በርካታ ሰዎችም ሥነ ሥርዓቱን ይታደማሉ።
ለምሳሌ ንግሥቲቱና ሟቹ መስፍን ፊሊፕ ትዳር የመሠረቱት በ1947 በዌስትምኒስትር አቤይ ነበር።
ዌስትሚኒስትር አቤይ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ960 የተመሰረተ ነው። ከፓርላማው አቅራቢያ የሚገኝም ነው።
በርካታ የንጉሣዊ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች የተደረጉበት ሥፍራም ነው። ባለፉት አንድ ሺህ ዓመታት ትልልቅ ጋብቻዎች የተደረጉበት እንዲሁም የትልልቅ ነገሥታት መቃብር የሚገኝበት ሥፍራም ነው።
ከንግሥቲቱና ከሟቹ ልዑል ፊሊፕ ጋብቻ ስድስት አስርት ዓመታት በኋላ በ2011 የልዑል ዊሊያምና የልዕልት ካተሪን ሚድልተን ጋብቻ የተፈጸመውም እዚሁ ነበር። የኬምብሪጇ ሶፋኒት ልዕልት ተብለው የተሰየሙትም በዚሁ ሥፍራ ነበር።
ሌሎች የንጉሣን ቤተሰቦች በዊንድሰር ጥንታዊ ቤተ መንግሥት ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ መቅደስ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል። ይህ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ 900 ዓመታትን ያስቆጠረ ነው።
የቅርብ ጊዜ ትዝታ የሆነውና ሚሊዮኖች የተከታተሉት የልዑል ሐሪ እና የሜጋን ማርክል የጋብቻ ሥነ ሥርዓትም እዚህ ነበር የተፈጸመው።
የንጉሣዊያን ቤተሰቦች የት ሆስፒታል ይወለዳሉ?
በርካታ የንጉሣዊያን ቤተሰቦች ምርጫ የለንደኑ ሴይንት ሜሪ ሆስፒታል ነው።
ልዕልት ዳያና ልዑል ዊሊያምንና ልዑል ሐሪን የተገላገለችው እዚህ ሆስፒታል ነበር።
የኬምብሪጇ ልዕልት ሦስት ልጆች፣ ልዑል ጆርጅ 7 ልጆች፣ ልዕልት ሻርለት አምስት ልጆች እና ልዑል የልዊስ ሁለት ልጆች የተወለዱትም እዚሁ ሴይንት ሜሪ ሆስፒታል ውስጥ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, PA
የንጉሣዊ ቤተሰቦች ተግባርና ኃላፊነት ምንድነው?
የብሪታኒያ መንግሥት የግርማዊነታቸው መንግሥት ተብሎ ነው የሚጠራው። ይህ ማለት ግን ንግሥቲቱ የጎላ የፖለቲካ ሥልጣን አላቸው ማለት አይደለም።
ንግሥቲቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሳምንት አንድ ቀን ይገናኛሉ። ይህም ንግሥቲቱ በመንግሥት ላይ ያላቸውን ቦታ እንደማሳያም እንደማስታወሻም የሚያገለግል ነው።
ያም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፖሊሲ ጉዳዮች የንግሥቲቱን ይሁንታ ማግኘት አያስፈልገውም።
ሌሎች አገሮች ጉብኝት ሲኖር ከንጉሣዊ ቤተሰቦች መካከል አንዳቸው ንግሥቲቱን ሊወክሉ ይችላሉ።
ለምሳሌ ባለፈው መጋቢት የኬምብሪጅ ልዑልና ልዕልቲቱ በአየርላንድ ሪፐብሊክ ጉብኝት ሲያደርጉ ይፋ ንጉሣዊ ጉብኝት ሆኖ ነው የተወሰደው።
ንጉሣዊ ቤተሰቦች ከቀጥታ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ይልቅ በብዛት በበጎ አድራጎት ሥራዎችና በተቋሞች የበላይ ጠባቂነት መደቦች ላይ ነው የሚሰማሩት።
አንዳንዶቹ የራሳቸው የበጎ አድራጎት ሥራ ድርጅትም አላቸው። ለምሳሌ ሟቹ ልዑል፣ የኤደንብራው መስፍን ፊሊፕ የወጣቶች የሽልማት ድርጅት መሥርተው ነበር።
ከመከላከያ ኃይሉ ጋር ቅርበት አላቸው። ለምሳሌ ልዑል ዊሊያም በአየር ኃይል ውስጥ አገልግሏል። ልዑል ሃሪ ደግሞ በጦር ሠራዊት ውስጥ ተሳትፎ ነበረው።
ንጉሣውያን ቤተሰቦች ምን ግዴታ አለባቸው?
ግዴታ የለባቸውም። ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ልዑል ሃሪ እና ሜጋን ከይፋዊ የንጉሣዊ ቤተሰብ ተሳትፎዎች ራሳቸውን ገሸሽ አድርገው በራሳቸው ገቢ እንደሚተዳደሩ ይፋ አድርገው ዓለም ጉድ ብሎ ነበር።
የባኪንግሃም ቤተመንግሥት ጥያቄያቸውን ተቀብሎ የክብር ንጉሣዊ ማዕረጎቻችንና መጠርያዎቻቸውንም እንደሚመልሱ አረጋግጧል። ለጥንዶቹ ይውል የነበረው ገንዘብ እና ማዕረግም ለሌሎች ንጉሣዊያን ቤተሰቦች ይተላለፋል።
ሃሪና ሜጋን የንጉሣዊ ቤተሰብን ገንዘብ፣ ስምና ጥቅማጥቅምን አንፈልግም ሲሉ የመጀመሪያዎቹ አይደሉም።
የዮርክ መስፍን የነበረው ልዑል አንድሩ በ2019 በተመሳሳይ ከንጉሣዊ ቤተሰቡ ራሱን አግልሏል።
ይህም የሆነው ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ከወሲብ ቅሌት ጥፋተኛው ጄፍሪ ኤፒስቲን ጋር ጓደኝነት እንዳለው ካመነ በኋላ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ንጉሣዊ ቤተሰቡ የገቢ ምንጭ ምንድነው?
በየዓመቱ የብሪታኒያ መንግሥት ለንግሥቲቱ አንድ ከፍተኛ ክፍያን ይፈጽማል። ይህም የ'ሶቨሪን ግራንት' ይባላል።
ለምሳሌ የዚህ ዓመት የሶቨሪን ግራንት መጠን 85.9 ሚሊዮን ፓውንድ ነበር። ይህ ገንዘብ ለንጉሣዊ ቤተሰቡ ወጪና ለቤተ መንግሥት እድሳቶች የሚውል ነው።
ልዑል ቻርለስ ደግሞ ከዱቺ ኦፍ ኮርንዎል ጠቀም ያለ ገንዘብ ይቀበላል፡፡ ዶቺ ኦፍ ኮርንዎል ገንዘብ የሚያስገባ በ14ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የነበረ የይዞታና የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ነው። ባለፈው ዓመት ብቻ 22.3 ሚሊዮን ፓውንድ ገቢ አምጥቷል።
የንጉሣዊያን ቤተሰቦች የት ነው የሚኖሩት?
የንግሥቲቱ ይፋዊ መቀመጫ የሚገኘው በመሀል ለንደን ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት ውስጥ ነው።
ብዙውን ጊዜ ንግሥቲቱ የሳምንቱን መጨረሻ ቀናትና የፋሲካ ማግስትን በዊንድሰር ካስል፣ በርክሻየር ነው የሚሳልፉት።
ሆኖም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ንግሥቲቱ በበርክሻየር ነው በቋሚነት እየኖሩ ያሉት። ባለቤታቸው ልዑል ፊሊፕም የሞቱት እዚያው ነው።
ልዑል ቻርለስ የሚኖረው በለንደን ከባኪንግሃም ቤተመንግሥት በቅርብ ርቀት በሚገኘው ክላርንስ ሐውስ ውስጥ ነው።
ልዑል ዊሊምና ካትሪን ደግሞ ብዙም ሳይርቁ ኬንሲግተን ቤተ መንግሥት ውስጥ ይኖራሉ።















