የጃክ ማ ኩባንያ አሊባባ በቻይና የ2.75 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ተጣለበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአለማችን ግዙፉ የበይነ መረብ የንግድ ኩባንያ አሊባባ በቻይና የ2.75 ቢሊዮን ዶላር ቅጣት ተጥሎበታል።
ይህ የገንዘብ መጠን ክብረወሰን ነው ተብሏል።
የቻይና ተቆጣጣሪዎች አሊባባ የገበያውን ስርዓት ለአመታት ያህል በበላይነትና በብቸኝነት የተቆጣጠረበት መንገድ ክፍተት አግኝተንበታል ብለዋል።
ኩባንያው በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ውሳኔውን እንደሚያከብርና እንደሚፈፅም አስታውቋል።
የገበያ ስርዓት ተንታኞች በበኩላቸው ይህ ቅጣት ቻይና በኢንተርኔት የግብይት ስርዓት የሚፈፅሙና ፤ አይነኬ ነን ብለው ለሚያስቡ ግዙፍ ኩባንያዎችን እንደማትተው ማሳያ ነው ተብሏል።
ኩባንያው ከቻይና ውጭ እውቅና እምብዛም ባይኖረውም በቻይና ግን አድራጊና ፈጣሪ እንደሆነ የቢቢሲው ዘጋቢ ሮቢን ብራንት ከሻንጋይ ይናገራል።
አሊባባ አማዞንና ኢቤይ የተሰኙት ኩባንያዎች በጥምረት እንደማለት እንደሆነ የቢቢሲ ዘጋቢ አክሏል።
የኢንተርኔት ንግድ ላይ በዋነኝነት የሚሰራው ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዘርፉን በማስፋት ብድር፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ክፍያ አፈፃፀሞችና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ነው ተብሏል።
ኩባንያው ቻይና የጣለችበት ቅጣት ከሁለት አመት በፊት ያገኘው ገቢ አራት በመቶ ያህል ይሆናል እንደሆነም ተዘግቧል።
የቻይና የገበያ ስርዓት ተቆጣጣሪዎች እንደሚሉት አሊባባ ውድድርን ለመግታትና ለማስቆም በሚል የተለያዩ ሁኔታዎችን ይጠቀም ነበር እንዲሁም ሌሎች ተወደዳዳሪዎች ከገበያው እንዲወጡ ሆን ብሎ ሰርቷል ይሉታል።
የኩባንያው መስራች ታዋቂው ጃክ ማ በአንድ ዝግጅት ላይ የቻይና ተቆጣጣሪዎች ፈጠራን እየገቱ ነው በማለት ትችት ያዘለ ንግግር አድርገው ነበር።
ከዚህም ጋር የተገጣጠመ በሚመስል መልኩ መንግሥት የባለሃብቱን የቢዝነስ አሰራር እየፈተሸና ጠበቅ ያለ ምርመራ መክፈቱን አሳወቀ።
ጃክ ማ በቻይና ውስጥ የተሳካላቸው ባለሃብትና የስራ ፈጣሪ ናቸው።
"ይህ ቅጣት በገበያው ላይ በበላይነትና በብቸኝነት የተቆጣጠረውን ኩባንያ አሰራር የሚያስቀር ይሆናል" በማለት ቦኮም ኢንተርናሽናል የተባለው ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ ሆንግ ሃዎ ተናግረዋል።
"በቻይና ከፍተኛ ስፍራ የተሰጠው ጉዳይ ነው። ገበያው በብቸኝነትና በበላይነት መቆጣጠሩ ጋር በተያያዘ ቅጣት እንዲጣልበት ብዙ ግፊቶች ነበሩ" ይላሉ።
ሌሎች የአገሪቷ ግዙፍ ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲሁ ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው ነው ተብሏል።
በባለፈው ወር አገሪቷ ያወጣችው ገበያ በብቸኝነት መምራትና መቆጣጠር ህጎች ጥሰዋል ያለቻቸውን 12 ኩባንያዎች ቀጥታለች።
ከነዚህም ኩባንያዎች መካከል ቴንሰንት፣ ባይዱ፣ ዲዲ ቹክሲንግ፣ ሶፍት ባንክ፣ ባይት ዳንስ ይገኙበታል።












