ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ እና የሱዳን የድንበር ፍጥጫ ወዴት እያመራ ነው?
ሱዳን እና ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ለም በሆነው ለእርሻ ተስማሚው አልፋሽቃ የድንበር አካባቢ ይገባኛል በሚል ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ ከገቡ ወራት ተቆጥረዋል።
ሁለቱ አገራት ተፋጥጠው በሚገኙበት በዚህ የድንበር ይገባኛል ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ ቢገልፁም የሁለቱ አገራት ሠራዊት ግን በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይሰማል።
ሱዳን በትግራይ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ በአካባቢው ያለው የኢትዮጵያ ጦር ለቅቆ ሲወጣ ስፍራውን መቆጣጠሯ በወቅቱ ተዘግቧል።
በፈረንጆቹ መጋቢት 20/2013 ሱዳን ትሪቢውን እንደዘገበው የሱዳንን አካባቢ ጥሰው ለመግባት የሞከሩ 200 ያህል የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ከሱዳን ጦር ጋር ተኩስ ገጥመው ሁለት ሰዎች ሞተዋል።
ቀደም ብሎም በመጋቢት 14/2013 ደግሞ ይኸው መገናኛ ብዙሃን የሱዳን ወታደሮች ኢትዮጵያውያን ታጣቂዎችን በማጥቃት መሳሪያ መማረካቸውንና የግብርና መሳሪያዎች መውሰዳቸውን ዘግቧል።
እነዚህ ግጭቶች እንዳሉ ሆነው ሁለቱ አገራት የድንበሩን ፍጥጫ በንግግርና ውይይት ለመፍታት ፈቃደኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሱዳን ጋር ጦርነት እንዳማይፈልጉ ሲናገሩ ሱዳን በበኩሏ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የቀረበውን የማሸማገል ጥያቄ ተቀብለዋለች።
የሱዳን ኢትዮጵያን ድንበር ግጭት የሚያቀጣጥለው ምንድን ነው?
ሱዳን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1902 የተፈረመው የአንግሎ-ኢትዮጵያ የካርታ ላይ ምልከታ ስምምነት አልፋሽቃ የእኔ መሆኑን በእርግጠኝነት ያሳያል ስትል ትገልጻለች።
አክላም በርካታ ኪሎ ሜትሮች የሚረዝመው የሁለቱ አገራት የድንበር አካባቢ በአግባቡ ባለመካለሉ ከ1980ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ድንበሩን ዘልቀው ይገባሉ ስትል ትከስሳለች።
የሱዳን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ድንበሩን ጥሰው ሲያልፉ እና ሰዎች ሲገደሉ፣ የአርሶ አደሮች እንስሳት ሲዘረፍ እና ሰዎች ሲታገቱ ችላ ብለዋል ተብለው ይወቀሳሉ።
በዚህም የተነሳ በርካታ ሱዳናውያን አርሶ አደሮች አልፋሽቃ አካባቢን ጥለው ለመሄድ መገደዳቸው ይነገራል።
ሁለቱ አገራት ለምን አሁን ጦራቸውን ወደ ድንበር አስጠጉ?
በታኅሣሥ 06/2013 የኢትዮጵያውያን ታጣቂዎች አልፋሽቃን እየጠበቁ የነበሩ የሱዳን ወታደሮች ላይ የደፈጣ ጥቃት አድርሰው አራት ሱዳናውያን ወታደሮች መሞታቸው ካርቱም በድንበሩ አካባቢ በርካታ ጦሯን እንድታሰፍር አድርጓታል።
ከአስራ አምስት ቀን በኋላ ታኅሣሥ 21/2013 ደግሞ ሱዳን አጨቃጫቂውን የድንበር አካባቢ ሙሉ በሙሉ መቆጣጣሯን ገለፀች።
ኢትዮጵያ የጦር ኃይሏ በትግራይ ክልል ውስጥ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ በነበረበት ወቅት ሱዳን በአልፋሽቃ አካባቢ ላይ ወረራ በመፈፀም የበርካታ ገበሬዎች ንብረት እንዲወድም ማድረጓን ዜጎችም መፈናቀላቸውን በመጥቀስ ትከስሳለች።
እንዲሁም ኢትዮጵያ በድንበር ፍጥጫው ውስጥ የሦስተኛ ወገን እጅ አለበት ስትል ትወነጅላለች።
በመጋቢት 07/2013 የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄነራል አብድል ፈታህ አል ቡርሐን ኢትዮጵያ አልፋሽቃ የሱዳን መሆኑን እስካልተቀበለች ድረስ ምንም ዓይነት ንግግር አይኖርም ብለው ነበር።
ቡርሐን "በኢትዮጵያ ወገን ይህ የሱዳን ግዛት መሆኑ ተቀባይነት አግኝቶ ድንበሩ እስካልተሰመረ ድረስ ከማንም ጋር አንደራደርም" ማለታቸው ተሰምቷል።
የሱዳን ሚዲያዎች ግጭቱን እንዴት ዘገቡት?
የሱዳን የአገር ውስጥ ጣቢያዎች፣ የሱዳን ዜና አገልግሎት (ሱና)፣ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣብያው፣ የሱዳን መከላከያ ኃይል ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግጭት ብዙ ጊዜ ባይዘግቡትም በግል የሱዳን መገናኛ ብዙሃን በኩል በሰፊው የሚዘገቡትን ደግሞ አያስተባብሉም።
የሱዳን መከላከያ ኃይል የፌስቡክ ገጽ የአገሪቱ ወታደሮች መሳሪያቸውን እያወዛወዙ የጀግንነት ሙዚቃ ተከፍቶ ሲጨፍሩ ያሳያል።
በየካቲት 04/2013 ሌተናል ጄነራል ያሲር አል አታ አልፋሽቃን በጎበኙበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙትን ወታደሮች "ስንዝር የሱዳን መሬትን እንዳትሰጡ" ሲሉ ተናግረዋል።
የሱዳን ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያ በአልፋሽቃ "ወረራ" ፈፀመች፤ እንዲሁም ግብጽ በማዕድን የበለፀገውን ሃላዬብ ትርያንግልን "ያዘች" ሲሉ ይጽፋሉ።
የኢትዮጵያና የኤርትራ መገናኛ ብዙሃንስ እንዴት ዘገቡት?
ኢትዮጵያውያን የድንበሩን ፍጥጫ እንደ ሱዳናውያን በሰፊው አይዘግቡትም። አብዛኛውን ጊዜ ስለአለመግባበቱ የሚጽፉ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሚጠቅሱት የሱዳን ሚዲያዎችን ነው።
ብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣብያም ሆነ የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ መገናኛ ብዙሃን በድንበር ይገባኛሉ ላይ ለመነጋገር በቅድሚያ "ሱዳን ወደነበረችበት ትመለስ" የሚሉ የመንግሥት ባለስልጣናትን ብቻ ሲጠቅሱ ይስተዋላል።
የኤርትራ ብሔራዊ ሚዲያ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ጠቅሶ ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግባቸውን "በእርጋታ እና በማስተዋል" እንዲፈቱ መጠየቃቸውን ዘግቧል።
ሱዳን ኤርትራ የኢትዮጵያን ጦር ለመርዳት በድንበሩ አካባቢ ጦሯ ሰፍሯል ስትል ወንጅላለች።
የድንበር ይገባኛል ግጭት የመቀስቀስ እድሉ ምን ያህል ነው?
በአሁኑ ወቅት ሱዳን እና ኢትዮጵያ በድንበር ይገባኛሉ የተነሳ ወደ ጦርነት የመግባት እድላቸው አነስተኛ ነው።
ሁለቱም አገራት በውስጣዊ አለመረጋጋት እየታመሱ ነው።
የኢትዮጵያ ጦር ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ በተቀሰቀሰው ግጭት የተወጠረ ሲሆን በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችም ያሉ የበርካታ ንፁሃንን ሕይወት የቀጠፉ ብሔር ተኮር ጥቃቶችን ለመቆጣጠር እየታገለ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በሚደረግ ጦርነት ካርቱም ዳግም የህወሓትን ቅሪቶችን እንዳታስታጥቅ እና መጠጊያ እንዳትሰጣቸው ትሰጋለች።
ሱዳን በአሁኑ ጊዜ የትግራይን ግጭት ሸሽተው ወደ ግዛቷ የገቡ ከ70 ሺህ በላይ ስደተኞችን ታስተናግዳለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መጋቢት 14/2013 በአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተገኙበት ወቅት "በአሁኑ ጊዜ ሱዳን ከጎረቤት አገር ጋር ጦርነት የምትገጥምበት ሁኔታ ላይ አይደለችም፤ የከፋ ችግር አለው። ኢትዮጵያም ብትሆን ከሱዳን ጋር ጦርነት ለመግጠም በርካታ [ውስጣዊ] ችግር አለባት" ብለው ነበር።
ሱዳን አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በሁለት እግሯ ጠንክራ አልቆመችም። አገሪቱ አሁንም ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሀብት ድቀት ላይ ትገኛለች።
በቅርብ ጊዜ እንኳ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ውድነት፣ በዳርፉር የተከሰተው አለመረጋጋት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሱዳንን ፈትረው ከያዟት ጉዳዮች መካከል ናቸው።
ቀጠናዊ ተፅዕኖው ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ከሱዳን እና ከግብጽ ጋር በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ላይ እስካሁን ይህ ነው የሚባል መቋጫ ላይ አልደረሰችም።
ሦስቱ አገራት ላለፉት አስር ዓመታት በግድቡ ላይ ሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።
ሱዳን በሕዳሴ ግድቡ ላይ ገለልተኛ ሆና የቆየች ቢሆንም የድንበር አለመግባባቱ ከተከሰተ በኋላ ግን አቋሟን ቀይራለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ወንዙን ተከትለው ለሚኖሩ 20 ሚሊዮን ሱዳናውያን የሕዳሴ ግድብ "ስጋት" መሆኑን ተናግረዋል።
ግብጽ ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት፣ አውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካ እና የአፍሪካ ሕብረት እንዲያደራድሩ ያቀረበችውን ጥያቄ ስትደግፈው ኢትዮጵያ ደግሞ ተቃውማዋለች።
የካቲት 23/2013 ሱዳንና ግብጽ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን ይህም ሁለቱ አገራት ከማንኛውም ጊዜ በላይ ወዳጅነታቸውን እያጠናከሩ ለመሆኑ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል።