ታዋቂው ሰባኪ ነብይ ቡሺሪ ለልጁ ሞት የአገሩን መንግሥት ተጠያቂ አደረገ

ሽቅርቅር የሆነው የማላዊ ዜጋው ሰባኪ ሼፐርድ ቡሺሪ ለስምንት ዓመት ሴት ልጁ ሞት መንግሥትን ተጠያቂ አደረገ።

ቡሽሪ ኢንላይትንድ ክርስቲያን ጋዘሪንግ የተሰኘ ቤተ እምነት ባለቤት ሲሆን በአፍሪካ ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉት።

ቡሺሪ የሴት ልጁ ኢዝራኤላ ሞት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ ባያደርግም፤ ነገር ግን የሕክምና ባለሙያዎች ከአገር ውጪ የተሻለ ሕክምና እንድታገኝ ነግረውት እንደነበር ገልጿል።

ነገር ግን ቤተሰቡ ወደ ኬንያ ለሕክምና እየሄደ ሳለ የማላዊ ባለሥልጣናት ከአገር እንዳይወጡ በመከልከላቸው አስፈላጊውን ሕክምና ሳታገኝ መቅረቷን ገልጿል።

በየካቲት ወር ከቤተሰብ አባላቱ መካከል ልጆቹ ራፋኤላ እና እስራዜላ፣ የወንድም ልጅ የሆነችው ኤስተር እና አማቹ ማግዳላይን ዝጋምቦ በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ ከሚገኘው የካሙዙ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በግል አውሮፕላን ሊጓዙ ሲሉ የማላዊ ባለሥልጣናት አግደዋቸዋል።

በወቅቱ ቡሺሪ ቤተሰቡ ኢዝራኤላን ለማሳከም ወደ ኬንያ ሊጓዙ እነደነበር ተናግሯል።

የቡሺሪ ጠበቆች ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከወሰዱ በኋላ የማላዊ መንግሥት ውሳኔውን ከቀናት በኋላ ቀልብሷል።

ነገር ግን ቡሺሪ የኬንያውን የሕክምና ጉዞ እርግፍ አድርጎ በመተው በማላዊ ባሉ የሕክምና ተቋማት የልጁን ሕክምና መከታተል ቀጠለ።

ዛሬ ሰኞ፣ የልጁን መሞት ይፋ ያደረገው ቡሺሪ በኢዝራኤላ ሞት እንደማያዝን ይልቁንም የሕይወት ጉዞዋን በልዩ ሁኔታ እንደሚያከብር ገልጿል።

ነብይ ቡሺሪ በደቡብ አፍሪካ ኢሲጂ የተሰኘ ቤተ እምነት ያለው ሲሆን በኅዳር ወር በገንዘብ ማጭበርበር እና ሕጋዊ ያልሆነ ገንዘብን ወደ ሕጋዊ መስመር በማስገባት በቀረበበት ክስ ቀርቦበት የዋስትና መብት እንደተሰጠው ወደ አገሩ ማላዊ ሸሽቷል።