ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዊዝ መተላለፊያ ለመርከቦች እንቅስቃሴ ክፍት ሆነ
ለሳምንት ያህል የስዊዝ ቦይን ዘግታ የነበረችው መርከብ ከቦታው ላይ መነሳቷንና መስመሩም ለእንቅስቃሴ ክፍት መደረጉን የግብጽ ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ከማክሰኞ ጀምሮ በአንዲት መርከብ የተዘጋው የሱዊዝ መተላለፊ መስመር ለመክፈት የተደረገው ጥረት ውጤት አስገኝቶ መርከቧ ከመተላለፊያው ላይ እንድትንቀሳቀስ ተደረጓል።
ባለስልጣናት ለቀናት የተዘጋው የሱዊዝ ቦይ ቅዳሜ ወይም እሁድ ይከፈታል በማለት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቆይቶ ዛሬ ጠዋት መስመሩን ለማስከፈት ችለዋል።
በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ መስተጓጎልን ያስከተለው የመተላለፊያው መዘጋት ለተጨማሪ በርካታ ቀናት ሊቆይ ይችላል ተብሎ ቢሰጋም በተደረገው ጥረት ግዙፏ የጭነት መርከብ እንድትንቀሳቀስ ተደርጎ መተላለፊያው ሊከፈት ችሏል።
ከማክሰኞ ጀምሮ የባሕር መተላለፊያ መስመሩን በአግድሞሽ ዘግታ የቆመችውን ግዙፏን የጭነት መርከብ ለማንቀሳቀስ ጥረት ሲደረግ ነበር።
በዚህም ሳቢያ በመተላለፊያው የሰሜንና የደቡብ መግቢያ መስመር ላይ የሱዊዝ ቦይ መከፈትን በሚጠብቁ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው መርከቦች መጨናነቅ መፈጠሩ ተገልጿል።
ጆ ሬይኖልድስ የታዋቂው የመርከብ እቃ አመላላሽ ድርጅት ሚርስክ ዋና ኢንጂነር ናቸው። ለቢቢሲ ሲገልጹ ''በቦዩ ደቡባዊ መግቢያ በኩል መንገዱ በመዘጋቱ በርካታ መርከቦች ለማለፍ እየተጠባበቁ ነው። ይህ ደግሞ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ፈጥሯል'' ብለዋል።
''በመላው ዓለም የተዘረጋው የመርከቦች የጉዞ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል'' ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ማክሰኞ ጠዋት አካባቢ 400 ሜትር ርዝማኔና 59 ሜትር ስፋት ያለው መርከብ ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት አሁንም ድረስ መንገድ እንደዘጋ ይገኛል።
የሱዊዝ ቦይ በመባል የሚታወቀው የግብፅ መተላለፊያ ሜድትራኒያን እና ቀይ ባሕርን በማገናኘት በእስያና አውሮፓ መካከል አጭሩ የሚባለውን የውቅያኖስ መንገድ ይፈጥራል።
በታይዋኑ ኤቨርግሪን ማሪን ሥር ያለው ኤቨር ጊቭን መርከብ በዓለም ትልቁ ኮንቴነር ጫኝ ሲሆን፤ 200,000 ቶን የሚመዝን እንዲሁም 20,000 ኮንቴነር ማጓጓዝ የሚችል ነው።
ኤቨር ግሪን የተሰኘው ግዙፍ መርከብ ከቻይና ተነስቶ ወደ ኔዘርላንድስ እያቀና ነበር። የግብፅ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት መርከቡ ባጋጠመው ቴክኒካዊ ችግር ምክንያት ነው መሀል ላይ ቆሞ የቀረው።
በፈረንጆቹ 2018 የተሠራው ይህ የፖናማ መርከብ ኤቨርግሪን ማሪን በተሰኘው የትራንስፖርት ኩባንያ ባለቤትነት ነው የሚንቀሳቀሰው።
በእንደዚህ አይነት ችግሮች ብዙ ልምድ አላቸው የተባሉ ድርጅቶች የሱዊዝ ቦይ ትራፊክ መጨናነቅን ለመፍታት ቢጥሩም እስካሁን መፍትሄ አልተገኘም።
የግብፅ ፕሬዝዳንት አማካሪ ችግሩ በቀናት ውስጥ እንደሚፈታ ገልጸው ነበር። ነገር ግን ባለሙያዎቹ ትልቋን መርከብ ለማንቀሳቀስና ወደቀደመው እንቅስቃሴ ለመመለስ ሳምንታት ሊፈጅ እንደሚችል ሲሉ ቆይተዋል።
መተላለፊያው በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ምርቶች የሚተላለፉበት ሲሆን፤ የጦፈ ንግድ የሚካሄድበት መስመር ነው። ከመላው ዓለም የባሕር ንግድም 12 በመቶው የሚያልፈውም በዚሁ የግብፅ የባሕር ላይ ማቋረጫ መስመር በኩል ነው።
በሱዊዝ ቦይ ምትክ እንደ አማራጭ የቀረበው የኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ መንገድ ደግሞ ከሱዊዝ ቦይ ጋር ሲነጻጸር ተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ይፈጃል። ይህ ደግሞ ለበርካታ የመርከብ ድርጅቶች አዋጪ አይደለም።
የግብፅ ሱዊዝ ቦይ በመዘጋቱ ምክንያት እስካሁን በየቀኑ 9.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች መተላለፍ አልቻሉም።
ሎይድስ ሊስት የተባለው የመርከብ ጉዞ ድርጅት እንደሚለው፤ በቀን ውስጥ ከምዕራብ አቅጣጫ ይመጡ የነበሩ 5.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች መጓጓዝ አልቻሉም። ከምሥራቅ አቅጣጫ ይመጡ የነበሩና የተስተጓጎሉ ምርቶች ደግሞ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ናቸው።
ሎይድስ ሊስት ባወጣው አሃዝ መሠረት፤ በአሁኑ ጊዜ 160 መርከቦች በሱዊዝ ቦይ በኩል ለማለፍ እየጠበቁ ነው። ከእነዚህ መካከል 41 የሚሆኑት የተለያዩ ምርቶች ሲይዙ 24 ደግሞ ነዳጅ ጫኝ ናቸው።
ቢአይኤምሲኦ የተባለው ዓለም አቀፍ የመርከበኞች ማኅበር እንደሚለው መተላለፊያው ተዘግቶ ከቆየ የምርት አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።
በተጨማሪም በሱዊዝ የመተላለፊያ መስመር ላይ ቆማ የባሕር ላይ ጉዞን ባስተጓጎለችው መርከብ የተነሳ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል። በመተላለፊያ መስመሩ መዘጋት ሰበብ የድፍድፍ ነዳጅ አቅርቦት ሊስተጓጎል ይችላል በሚል ስጋት ነው ረቡዕ ዕለት የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የታየበት።
በሰሜናዊ ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኘውን ወሳኝ የባሕር ላይ መተላለፊያን ዘግታ የምትገኘው የጭነት መርከብ ባለቤት የሆነው ጃፓናዊ በመርከቧ ምክንያት በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ለተፈጠረው መስተጓጎል ይቅርታ መጠየቁ ተነግሯል።
በከባድ ንፋስ ምክንያት መስመሯን ስታ መተላለፊያውን የዘጋችውን መርከብ ለማንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ የገለጸው የመርከቧ ባለቤት "ነገር ግን የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ" ላይ መሆናቸውን ገልጿል።