ሱዊዝ ቦይ በመዘጋቱ በየቀኑ የ9.6 ቢሊዮን ዶላር ምርት መተላለፍ አልቻለም

የግብጹ ሱዊዝ የባሕር ላይ ማቋረጫ ቦይ በመዘጋቱ በየቀኑ 9.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች መተላለፍ እንዳልቻሉ ተገለጸ።

በሱዊዝ መተላለፊያ ላይ አንድ ግዙፍ የጭነት መርከብ ባሕሩን ዘግቶ ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ በመቆሙ ምክንያት እንቅስቃሴ መገታቱ ይታወሳል።

ሎይድስ ሊስት የተባለው የመርከብ ጉዞ ድርጅት እንደሚለው፤ በቀን ውስጥ ከምዕራብ አቅጣጫ ይመጡ የነበሩ 5.1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች መጓጓዝ አልቻሉም። ከምሥራቅ አቅጣጫ ይመጡ የነበሩና የተስተጓጎሉ ምርቶች ደግሞ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ናቸው።

የባሕሩን መተላለፊያ የዘጋው መርከብ እንቅስቃሴ እንዲጀምር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ሳምንታት ሊወስድ እንደሚችል ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በታይዋኑ ኤቨርግሪን ማሪን ሥር ያለው ኤቨር ጊቭን መርከብ በዓለም ትልቁ ኮንቴነር ጫኝ ሲሆን፤ 200,000 ቶን የሚመዝን እንዲሁም 20,000 ኮንቴነር ማጓጓዝ የሚችል ነው።

መርከቡ በመቆሙ ሳቢያ ሌሎች መርከቦች ለቀናት መተላለፍ አልቻሉም።

የባሕር ላይ ጉዞ አማካሪ ድርጅት ባለቤት ጆን ሞንሮይ ብዙ ወደቦች ላይ የሚገኙና መጓጓዝ ያልቻሉ ኮንቴነሮች እንዳሉ ይናገራል።

መተላለፊያው በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ምርቶች የሚተላለፉበት ሲሆን፤ የጦፈ ንግድ የሚካሄድበት መስመር ነው።

ከመላው ዓለም የባሕር ንግድም 12 በመቶው የሚያልፈውም በዚሁ የግብጽ የባሕር ላይ ማቋረጫ መስመር በኩል ነው።

ሎይድስ ሊስት ባወጣው አሃዝ መሠረት፤ በአሁኑ ጊዜ 160 መርከቦች በሱዊዝ ቦይ በኩል ለማለፍ እየጠበቁ ነው። ከእነዚህ መካከል 41 የሚሆኑት የተለያዩ ምርቶች ሲይዙ 24 ደግሞ ነዳጅ ጫኝ ናቸው።

ቢአይኤምሲኦ የተባለው ዓለም አቀፍ የመርከበኞች ማኅበር እንደሚለው መተላለፊያው ተዘግቶ ከቆየ የምርት አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም።

የሎጂስቲክስ ተቋሙ ኦኤል ዩኤስኤ ፕሬዘዳንት አለን ባይር "በእያንዳንዱ ቀን ያልተጓጓዙ ምርቶችን ለማሳለፍ ተጨማሪ ሁለት ቀናት ይጠይቃል" ብለዋል።

እስካሁን ለሦስት ቀናት መተላለፍ ያልቻሉትን ምርቶች ለማጓጓዝ ስድስት ቀናት ገደማ ሊያስፈልግ እንደሚችልም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

መተላለፊያው እስኪከፈት ድረስ ቀናት ወይም ሳምንታት ሊወስድ እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በመላው ዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጫና ያሳድራል።

የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ይህ የግብጽ የባሕር ላይ መተላለፊያ ከመዘጋቱ በፊት በኮቪድ-19 ምክንያት መቀዛቀዝ አጋትሞት ነበር።

አለን እንደሚሉት፤ መርከቦች ሌላ አማራጭ የጉዞ መስምር ከፈለጉ በምዕራብ አፍሪካ በኩል በመዞር ጉዟቸውን ሊቀጥሉ ብችሉም ይህ ጉዞ ግን ከሰባት እስከ ዘጠኝ ቀናት ሊፈጅ ይችላል።

አንዳንድ ተቋሞች መተላለፍ ባልቻሉ ምርቶቻቸው ምትክ ሌሎች ምርቶችን በአውሮፕላን ወይም በባቡር መላክን እንደ አማራጭ ሊወስዱ ይችላሉ።

እስካሁን ድረስ ሜርስክ እና ሀፓግ ሎይድ የተባሉ ተቋሞች ከሱዩዝ መተላለፊያ መስመር ውጪ ያሉ አማራጮችን እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።

የግብጹ የሱዊዝ መተላለፊያ ባለሥልጣን ባሕሩን የዘጋውን መርከብ ለማስነሳት የቻለውን ሁሉ እየሞከረ እንደሆነ አስታውቋል።