በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ

በኢትዮጵያ ውስጥ ምርመራ አድርገው የኮሮረናቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ ሆነ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበሽታው መስፋፋት ፍጥነት እየጨመረ ከመጣ በኋላ በየቀኑ የሚመዘገበው ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

በዚህም መሠረት ትናንት እሁድ ምርመራ ከተደረገላቸው 7,250 ሰዎች መካከል ቫይረሱ በ1,769 ሰዎች ላይ በመገኘቱ በአገሪቱ በወረርሽኙ የታያዙ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ እንዲሆን አድርጎታል።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ ከተረጋገጠበት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ምርመራ ካደረጉ ከ2,332,735 ሰዎች መካከል መካከል በ200,563 ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።

በሽታው እንዳለባቸው ከተረጋገጡት ሰዎች ውስጥ ደግሞ 2,801 ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን፤ በጽኑ የሚታመሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከዕለት ዕለት እያሻቀበ መሆኑን ስለበሽታው የሚወጣው ዕለታዊ መረጃ ያመለክታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባለፉት ሳምንታት የሚወጡት የወረርሽኙ መግለጫዎች ያመለከቱ ሲሆን የበሽታው መስፋፋት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።

በዚህም ሳቢያ በበሽታው በየዕለቱ የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከነበረው በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል።

በጽኑ ታምመው የህክምና ድጋፍ የሚፈልጉ ህሙማን ቁጥርም በማሻቀቡ የህክምና ተቋማት ያላቸው የማስተናገድ አቅም መፈተኑን፣ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያና የኦክስጂን አቅርቦት እጥረት ማጋጠሙም ባለፈው ሳምንት መገለጹ ይታወሳል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በተከታታይ የሚያወጣቸው መረጃዎች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከተመዘገበው በላይ በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በበሽታው የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸውን ያሳያል።

ከዚህ አንጻርም ከመጋቢት 11 አስከ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም በተደረገ ምርመራ 12‚758 ግለሰቦች ላይ የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን፤ በእነዚሁ ቀናት ውስጥ 151 ግለሰቦች በወረርሽኙ ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ በወረርሽኝ ተይዘው የጽኑ ህሙማን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ሲሆን፤ የህክምና ተቋማቱ ካላቸው የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያና ግብዓት አቅርቦት አንጻር ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ የተወሰኑት ድጋፉን ለማግኘት ወረፋ ለመጠበቅ መገደዳቸው ተገልጿል።

በዚህም ሳቢያ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ከወራት በፊት ወጥቶ የነበረው መመሪያ በጥብቅ ተግባራዊ እንዲሆን ተወስኗል።