ቴክኖሎጂ፡ የዓለም ቋንቋዎችን በአጠቃላይ የሚተረጉም ቴክኖሎጂ እውን ይሆናል?

ጉግል

በዓለም ላይ ከ7 ሺህ በላይ ቋንቋዎች አሉ። 4 ሺህ ያህሉ የጽሑፍ ፊደላት አሏቸው። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ጉግል የሚተረጉማቸው ወደ 100 የሚጠጉትን ነው።

ውልፍ፣ ሉጋንዳ፣ ትዊ እና ሌሎችም በርካታ ቋንቋዎችን የሚተረጉም መተግበሪያ እስካሁን የለም።

እነዚህ ቋንቋዎች በዋነኛነት ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የሚተረጎሙት በቋንቋው ተናጋሪዎች አማካይነት ነው።

ቴክኖሎጂን ያማከለ የትርጉም አገልግሎት ከሚሰጡ አንዱ ጉግል ነው። ጉግል 108 ቋንቋዎችን ይተረጉማል። ማይክሮሶፍት ደግሞ 70 ቋንቋዎችን።

መረጃን በፍጥነት መለዋወጥ አስፈላጊ በሆነበት ዓለም ከ4,000 በላይ ቋንቋዎችን በመተግበሪያ መተርጎም አለመቻል የመረጃ ፍሰትን ማጓተቱ አይቀርም።

በአሜሪካ የደህን ነት ምርምር ተቋም የሚሠራው ካርል ሩቢኖ እንደሚለው፤ በቋንቋ መግባባት አለመቻል በፓለቲካና በምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ክፍተት ይፈጥራል።

አንድን ሰው አዲስ ቋንቋ ማስተማር ጊዜ ይጠይቃል። ለምሳሌ በናይጄሪያ ከ500 በላይ ቋንቋ ይነገራል።

ካርል የሚሠራበት ተቋም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ጥናት ጀምሯል። ጥናቱ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚደረግ ንግግርን ወይም ጽሑፍን መተርጎም የሚችል አሠራር መፍጠር ላይ ያተኩራል።

በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ምሁሯ ካትሊን ማኮን፤ ይህንን ቴክኖሎጂ መተግበር ከተቻለ በርካቶች በቀላሉ ሊግባቡ የሚችሉበት ቀን ሩቅ አይሆንም ትላለች።

አጥኚዎቹ ሰው ሠራሽ ክህሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) በመጠቀም ልክ እንደ ሰው የሚያስብ መሣሪያ ለመሥራት ነው ሐሳባቸው።

መሣሪያው ቃላትን ከማወቅ ባሻገር ትርጉማቸውንም የሚገነዘብ ይሆናል። በእርግጥ አንዳንዴ ከአውድ ውጪ የሆነ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል።

ማሽን ቋንቋዎችን ተረድቶ እንዲተረጉም ለማስቻል በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ገጾች የተዘጋጀ ጽሑፍን ማስተማር የመጀመሪያው ደረጃ ነው። ሂደቱ ቀላል አይደለም።

የኤምአይቲዋ ኮምፒውተር ሳይንቲስት ረጂና ባርዝሊ "ማሽን ቋንቋ ሲማር፤ ሰው ቋንቋ ሲማር ማወቅ ከሚጠበቅበት መረጃ በላይ ይሰጠዋል" ትላለች።

ቴክኖሎጂው እውን ከሆነ ቀጣዩ ትውልድ ምናልባትም አስተርጓሚዎች ላያስፈልጉት ይችላሉ።

ማሽኑ የቃላት ትርጉም መፈለጊያ ክፍል፣ ድምጽ ሰምቶ የሚተረጉም ክፍል እንዲሁም ሌሎችም ይዘቶች አሉት። አጥኚዎች ከጎርጎሮሳውያኑ 2017 ጀምሮ እያንዳንዱን ይዘት ተከፋፍለው ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ።

በጥናቱ ከተካተቱ ቋንቋዎች መካከል ስዋሂሊ፣ ታጋሎግ፣ ሶማሊ እና ካዛክ ይጠቀሳሉ።

አንዱ የጥናቱ ትኩረት ዜና፣ ቪድዮ እና ሌሎችንም ማሽኑ እንዲተረጉም ማስቻል ነው።

በሳውዘርን ካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲ የኮምፒውተር ሳይንቲስቱ ስኮት ሚለር እንደሚለው፤ ብዙዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ጽሑፎችና ቪድዮዎች ድረ ገጽ ላይ መለጠፋቸው ለምርምሩ ረድቷል።

ማሽኑ አንድን ቋንቋ ወደሌላ ቋንቋ እንዲተረጉም ይደረጋል። ለምሳሌ ከስዋሂሊ ወደ እንግሊዘኛ መተርጎም። በቀጣይ ደግሞ የትኛውንም ቋንቋ ወደመተርጎም ይሸጋገራል።

አንድ ሰው ትርጉም ሲፈልግ ማሽኑን በጽሑፍ ወይም በድምጽ መጠየቅ ይችላል።

ተመራማሪዎቹ የአንድ ሰው ስም በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንዴት እንደሚነበብ ወይም ሌላ ከቋንቋ ጋር የተያያዘ መረጃ ሲፈለግ በቀላሉ እንዲገኝ ማስቻል አስበዋል።

የኢዲንበጓ ኮምፒውተር ሳይንቲስት ሚርላ ላፓታ አንድ ጽሑፍን ሙሉ በሙሉ ለመተርጎም ከመሞከር ይልቅ በቁልፍ ቃላት ከፍሎ መተርጎም ይቀላል ትላለች። ይህንን ለማሽኑ ለማስተማርም እየሞከች ነው።

ማሽኑ እውን ከሆነ አሁን ላይ ሰዎች ከሚግባቡባቸው ቋንቋዎች ባሻገር ቀደምትና የጠፉ ቋንቋዎችን ለማጥናትም ታስቧል።

ጥንታዊ ቋንቋዎች በግንባር ቀደምትነት የሚገኙት በጽሑፍ ስለሆነ ጥናቱ ቀደምት መዛግብት ላይ ያተኩራል።

አሁን ላይ ማሽኑ የተለያዩ ቋንቋዎችን ትርጉም ለመፈለግ የሚውለው (ሰርች ኢንጅን) ተሠርቷል።

የጥናቱ መሪ እንደሚለው፤ ከደህንነት ጥበቃ ጋር የተያያዙ እንደ ስለላ ያሉ ሥራዎችን ጨምሮ ማሽኑ በተለያዩ ዘርፎች አገልግሎት ላይ ይውላል።

የሕክምና ተማሪው ዴቪድ ኢፍልዋ አድላኒ እንደሚለው፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሲነሳ በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ መረጃዎችን መተርጎም አስፈላጊ ሆኗል። በተለይም በቀላሉ አስተርጓሚ ማግኘት ባልተቻለባቸው ሁኔታዎች ነገሮች ፈታኝ ነበሩ።

"እንደ ወረርሽኙ ያሉ አስቸኳይና አንገብጋቢ ሁነቶች ሲፈጠሩ የትርጉም መተግበሪያ የግድ ያስፈልገናል" ይላል።

ናይጄሪያዊው ዴቪድ የዩርባ ቋንቋ ተናጋሪ ነው።

ዴቪድ ዮርባ ወደ እንግሊዘኛ የሚተረጉም መተግበሪያ የሚሠራ ቡድን አባል ነው። የፊልም ጽሑፍ፣ ዜና፣ ንግግር እና ሌሎችም ጽሑፎችን በመሰብሰብ ነው መተግበሪያውን ያበለጸጉት።

ሃይማኖት የሚያስተምሩ ጽሑፎችንም የተጠቀሙ ሲሆን፤ ኢዊ፣ ፎንግቤ፣ ትዊ እና ሌሎችም የአፍሪካ ቋንቋዎችን የሚተረጉም ዳታቤዝ የመሥራትም እቅድ አላቸው።

ማሽኑን እውን ለመሆን ያብቃው እንጂ፤ ማንኛውንም ቋንቋ በቀላሉ የምንተረጉምበት፣ በቀላሉ መረጃ የምንለዋወጥበት፣ የማናውቀውን ቋንቋ ከሚናገር ሰው ጋር የምንግባባት ቀን ሩቅ አይመስልም።