ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የማሌዥያ ፍርድ ቤት ክርስቲያኖች 'አላህ'ን የአምላካቸው መጠሪያ ማድረግ ይችላሉ አለ
የማሌዥያው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክርስቲያኖች አምላካቸውን ለመጥራት ሲፈልጉ 'አላህ' የሚለው ቃል መጠቀም አይችሉም የሚለውን ፖሊሲ ከሰሞኑ ቀልብሷል።
ጉዳዩ ለአስርት አመታትም ያህል ያከራከረ ነው ተብሏል።
የእስልምና እምነት ተከታይ ያልሆኑ ሰዎች "አላህ" የሚለውን ቃል መጠቀም ጉዳይ ማሌዥያን ለውጥረት ዳርጓታል።
ከዚህ ቀደምም በርካታ ግጭቶችም ተነስተዋል።
በአገሪቱ ውስጥ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲሆን 2/3ኛውንም ይይዛሉ ተብሏል።
ነገር ግን ቀላል የማይባል የክርስትና እምነት ተከታይ ነዋሪዎችም አሉ።
የክርስቲያኑ ማህበረሰብ እንደሚከራከሩት ለዘመናት ያህል ከአረብኛ ተወስዶ በአገሬው ቋንቋ ማሌይ የተወረሰውን "አላህ" የሚለውን ቃል አምላካቸውን ለመግለፅ ሲጠቀሙበት እንደኖሩ ነው።
ክልከላውም "መብታችንን ይጥሳል" በማለት ሲከራከሩ ነበር።
የማሌዥያ ህገ መንግሥት የእምነት ነፃነት ላይ ግልፅ ያለ ህግ ቢኖረውም በቅርብ አመታት በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ውጥረት እንደነገሰ ይነገራል።
ህገወጥና ኢ-ህገመንግሥታዊ ነው
በአውሮፓውያኑ 2008 የማሌዥያ ባለስልጣናት የማሌይ ቋንቋ የሰፈረበት ሲዲ ጂል አየርላንድ ላውረንስ ከምትባል ርስቲያን ግለሰብ ወሰዱ።
በሲዲው ላይ አላህ የሚል ቃል የሰፈረበት ሲሆን በወቅቱም አየር ማረፊያ ላይ ነበረች ተብሏል።
ይህቸው ግለሰብ በአውሮፓውያኑ ክርስቲያኖች አላህ የሚለውን ቃል በህትመቶቻቸው መጠቀም አይችሉም የሚለውን ህግ ለማስቀየር ክስ ከፈተች።
ከአስር አመታት በኋላ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ የኩዋላ ላምፑር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግለሰቧ በእምነቷ ምክንያት ልትገለል አይገባም ፤ የሃይማኖት ነፃነቷም ሊከበር ይገባል የሚል ውሳኔን አስተላለፈ።
ዳኛ ኖር ቢ ባስተላለፉት ውያኔ መሰረት አላህ የሚለውን የአረብኛ ቃል ጨምሮ 'ካባህ' (በመካ የሚገኝ ቅዱስ ቦታ)፣ ባይቱላህ (ቤተ መቅደስ)ና ሰላት (ፀሎት) የሚሉ ቃላቶችን ክርስቲያኖች መጠቀም ይችላሉ ብለዋል።
ዳኛዋ ውሳኔውን ባስተላለፉበት ወቅት እነዚህን ቃላቶች መጠቀም ያገደው አዋጅ "ህገ ወጥና ኢ-ህገመንግሥታዊ ነው" ብለዋል።