ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያ ፀጉረ ልውጥ ውሾች
የፀጉራቸው ቀለም ከተለመደው ውጪ የሆኑ ውሾች በሩሲያ ታይተዋል። በቅድሚያ ደማቅ ሰማያዊ ውሻ፣ ከዚያ ደግሞ ደማቅ አረንጓዴ።
ሩሲያ የእነዚህን አጃሂብ ያሰኙ ውሾች ቀለም ምክንያት ለማጣራት ተፍ ተፍ እያለች ነው።
በርግጥ ውሾቹ የተገኙት በበርካታ ማይሎች ርቀት በሚገኙ የኢንደስትሪ መንደሮች አካባቢ ነው።
ደማቅ ሰማያዊ ፀጉር ያላቸው ውሾች ወዲያ ወዲህ ሲሉ የተገኙት በአንድ መስታወት ፋብሪካ አካባቢ ነበር።
ፋብሪካው የሚገኘው ዜርዚኒስክ በሚባል ግዛት ሲሆን ከሞስኮ በምስራቅ በኩል 370 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ከአስር ቀን በፊት አንድ የአካባቢው መገናኛ ብዙኀን የእነዚህን ፀጉረ ልውጥ ውሾች ምስል ካጋራ በኋላ፣ ሰዎች እየተቀባበሉት ጉዳዩን መነጋገሪያ አድርገውታል።
ፋብሪካው አክረሊክ መስታወት እና ፕሩሲክ አሲድ ያመርታል። እንግዲህ የተመራማሪዎቹ የመጀመሪያ መላ ምት ውሾቹ ከፋብሪካው በወጣ እና ሰማያዊ ቀለም ባለው ዱቄት ላይ ተንደባለዋል የሚል ነው።
ከሰባት ቀን በፊት ውሾቹ ወደ እንስሳት ሀኪም ዘንድ እንዲመጡ የተደረገ ሲሆን፣ የደምና የሰገራ ናሙናቸው ተወስዶ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
በቆዳቸው ላይ ሰማያዊ ፕሩሲያን ብናኝም ተገኝቷል።
የሩሲያ መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ውሾቹ ጤናማ ሲሆኑ፣ በተገቢው ሁኔታም እየተመገቡ ነው።
ይኹን እንጂ አሁንም እንደ ኮፐር ሰልፌት ያለ መርዛማ ኬሚካል የፀጉራቸውን ቀለም ቀይሮት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ሐሙስ ዕለት ደግሞ በርካታ ደማቅ አረንጓዴ ፀጉር ያላቸው ውሾች በፖዶልስክ የኢንዱስትሪ ከተማ ወዲያ ወዲህ ሲሉ ተስተውለዋል።
ይህ የኢንዱስትሪ ከተማ ከሞስኮ በ37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።
የሞስኮ ክልላዊ ሚኒስተር ውሾቹ የታዩት ባዶውን የተተወ አንድ መጋዘን አካባቢ ነው ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ በመጋዘኑ አረንጓዴ ቀለም ዱቄት ተከማችቶ ይገኛል።
ነገር ግን ለአንዳንድ ሩሲያውያን ይህ የሚዋጥ ነገር አልሆነም።
ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ውሾች የበርካታ ሰዎችን ቀልብ ስበው ስለነበር እንዲሁ ዋዛ ፈዛዛ ወዳድ አረንጓዴ ቀብቷቸው ሊሆን ይችላል ሲሉ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የእንስሳት ሀኪሞች እነዚህንም የፖዶልስክ ውሾችም የመረመሩ ሲሆን እስካሁን ድረስ ፀጉራቸው ለምን አረንጓዴ እንደሆነ የተጣራ መረጃ አልተገኘም።
ነገር ግን ልክ እንደ ዜርዚንስክ ውሾች ሁሉ እነዚህም ጤናማ መሆናቸው ተረጋግጧል።
የሁለቱንም ውሾች ፀጉር ቀለም የቀየረው ምንም ይሁን ምን በሩሲያ በኮሙኒዝም ጊዜ የተገነቡ እና ያረጁ ፋብሪካዎች አሁንም ለኬሚካል ብክለት አሳሳቢ መሆናቸውን አስታዋሽ ሆነዋል።