ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትምኒት ገብሩ መባረር የተተቸው ጉግል ሌላ ባለሙያ አባረረ
ጉግል ከወራት በፊት የሰው ሠራሽ ክህሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) የሥነ ምግባር ክፍል ባለሙያ የሆነችው ትምኒት ገብሩን (ዶ/ር) በማባረሩ ሲተች ነበር። አሁን ደግሞ ማርጋሬት ሚቼል የተባለች ሌላ ባለሙያ አባሯል።
ማርጋሬት የሰው ሠራሽ ክህሎት ክፍሉ፣ የሥነ ምግባር ቅርንጫፍ መስራች ናት።
ጉግል ማርጋሬት የተባረረችው የጉግልን መርህ በመጣስ፣ ከድርጅቱ ሰነድ ስላወጣች ነው ብሏል።
ባለፈው ጥቅምት ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) ከተባረረች ወዲህ፤ የጉግል የሥነ ምግባር ክፍል አያያዝ በጣም እየተወገዘ ነው።
ትምኒት (ዶ/ር) እና ማርጋሬት ድርጅቱ አካታች መሆን አለበት በሚል ንቅናቄ ይታወቃሉ። ድርጅቱ ሠራተኞቹን ሳንሱር እንደሚያደርግም ቅሬታ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
ማርጋሬት "ከሥራ ተባርሬያለሁ" ስትል በትዊተር ገጿ አስታውቃለች። የጉግል ኢሜሏን እና ቀን መቁጠሪያዋን እንዳትጠቀም ለአምስት ቀናት ጉግል አግዷታል።
በሰላ ሂስ የምትታወቀው ማርጋሬት፤ ትምኒት (ዶ/ር) ከተባረረች በኋላ ለጉግል ቅሬታ አቅርባለች።
ትምኒት (ዶ/ር) ጉግል ከሥራዋ ያባረራት ድርጅቱ ውስጥ ያለውን መድልዎ በመተቸቷ እንደሆነ ገልጻ ነበር። እየሠራች የነበረውን ጥናት ጉግል ለማስቆም ሲሞክር፤ ከጥናቱ ስሟ እንዲወጣ ስትጠይቅ፤ ጉግል ድርጅቱን በገዛ ፍቃዷ የለቀቀች አስመስሎ እንዳባረራት ተናግራለች።
የትምኒት (ዶ/ር) መባረር በርካታ የሰው ሠራሽ ልህቀትና ባለሙያዎችና ሌሎችም በቴክኖጂው ያሉ ሙያተኞችን አስቆጥቷል። የጉግል ሰው ሠራሽ ልህቀት ሥነ ምግባርንም ጥያቄ ውስጥ ከቶታል።
ጉግል አካታች አይደለም የሚል ትችት በተደጋጋሚ ይሰነዘርበታል።