በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት ፊቱን ወደ አሳማ እርባታ ያዞረው ሁዋዌ

ሁዋዌ በአሜሪካ ዘመናዊ ስልኮቹ ላይ ከባድ ማዕቀቦችን በመጣሉ ምክንያት ፊቱን ለአሳማ ገበሬዎች ቴክኖሎጂ ወደ ማቅረብ አዙሯል።

ግዙፉ የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ የትራምፕ አስተዳደር ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አስጊ ነው ተብሎ በመፈረጁ አስፈላጊ ዕቃዎችን እንዳያገኝ ተደርጓል፡፡

ሁዋዌ የገጠመውን የስማርት ስልክ ሽያጭ ሊያካክስ በመፈለጉ ለቴክኖሎጂው ሌሎች የገቢ ምንጮችን እየተመለከተ ነው፡፡

ለአሳማ ገበሬዎች በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጅ ከመሥራት በተጨማሪ ሁዋዌ የከሰል ማዕድን ኢንዱስትሪ ጋርም ይሠራል፡፡

ሁዋዌ የደንበኞችን መረጃ ለቻይና መንግስት ሊያጋራው ይችላል ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ክስ ቢያቀርቡትም ድርጅቱ በተደጋጋሚ አስተባብሏል፡፡

በዓለም ትልቁ የቴሌኮም መሣሪያዎች አምራቹ በዚህ ምክንያት የ 5ጂ ሞዴሎችን አካላት ለማስመጣት የአሜሪካ መንግሥት ፈቃድ ስለላልሰጠው የ 4ጂ ሞዴሎችን በመሥራት ተገድቧል፡፡

በብሔራዊ ደህንነት ላይ ስጋት ፈጥሮብናል ያሉ እንደ እንግሊዝ ያሉ ሌሎች ሃገራትም ሁዋዌ የሚያደርገውን የ 5ጂ ዝርጋታ አስቁመዋል፡፡

በዚህ ዓመት የስማርት ስልኮችን ምርቱን እስከ 60% ድረስ እንደሚቀንሰው ሪፖርቶች ጠቁመዋል፡፡ ይህን ግን ማረጋገጥ አልተቻለም።

"ይህ የሚያሳየው የሁዋዌ ምርቶች ጥራትና ልምዳችን ምንም አይነት ችግር እንደሌለበት ነው፡፡ ሁዋዌ በጂኦፖለቲካዊ ውዝግብ መካከል የተያዘ በመሆኑ ለሁዋዌ የመጫወቻ ሜዳው አይደለም" ሲሉ የኩባንያው ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስለዚህ ሁዋዌ ፊቱን ወደ ሌሎች የገቢ ምንጮችን ያዞረ ይመስላል። እንደክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ስማርት ተሽከርካሪዎች እና ተለባሽ መሣሪያዎች እንዲሁም ስማርት መኪና የማምረትም ዕቅዶች አሉት።

በጥቂት ተጨማሪ ባህላዊ ኢንዱስትሪዎች ላይ ዓይኑን ጥሏል፡፡

የአሳማ እርባታ

ቻይና በዓለም ትልቁ የአሳማ እርሻ ኢንዱስትሪ ባለቤት ስትሆን፣ የአለማችን አሳማዎች ግማሽ ያህሉ መኖሪያ ናት፡፡

በሽታዎችን ለመለየት እና አሳማዎችን እንቅስቃሴ ለመከታተል በሚያስችለው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አማካኝነት የአሳማ እርሻዎችን ለማዘመን ቴክኖሎጂው እየረዳ ነው፡፡

የፊት መለያ ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን አሳማዎች መለየት ሲያስችል ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ደግሞ ክብደታቸውን፣ አመጋገባቸውን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎቻቸውን ይቆጣጠራሉ፡፡

ሁዋዌ የፊት ለይቶ የማወቅ ቴክኖሎጂ በማዘጋጀት ላይ ሲሆን ባለፈው ወር ግን ትችት ገጥሞታል። ምክንያቱ ደግሞ ከእግረኞች ምስል መካከል የኡሂጉር ተወላጅ የሆኑ የሚመስሉትን ሰዎችን ለይቶ በሚያሳውቀው ስርዓቱ ነው።

እንደ ጄዲዳትኮም፣ አሊባባን ጨምሮ ሌሎች የቻይና ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከአሳማ ከሚያረቡ አርሶ አደሮች ጋር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ እየሠሩ ነው፡፡

የሁዋዌ ቃል አቀባይ አክለውም "በ 5ጂ ዘመን ለኢንዱስትሪዎች የበለጠ እሴት ለመፍጠር አንዳንድ ባህላዊ ኢንዱስትሪዎችን በኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) እንደገና ለማነቃቃት የምንሞክርበት ሌላ ምሳሌ ነው" ብለዋል፡፡

የከሰል ማዕድን እና መረጃ

የሁዋዌ መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሬን ዤንግፈይ በዚህ ወር መጀመሪያ በሰሜን ቻይና ሻንሺ ግዛት የማዕድን ፈጠራ ቤተ-ሙከራ በይፋ አስጀምረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለድንጋይ ከሰል ማዕድን አውጪዎች "አነስተኛ ሠራተኞችን፣ ከፍተኛ ደህንነትን እና ከፍተኛ ብቃትን የሚያመጣ እና ማዕድን አውጪዎቹ በሥራ ቦታቸው ሱፍ እና ከረቫት እንዲለብሱ" የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂን ለማዳበር ይፈልጋሉ፡፡

በዝግጅቱ ላይ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ በተደረገ ስብሰባ ላይ ሬን ኩባንያው ከሰል ማዕድን እና ከብረት እንደ ቴሌቪዥኖች፣ ኮምፒውተሮች እና ታብሌቶች ያሉ ምርቶች ላይ ትኩረት እያደረገ ይገኛል፡፡

"በስልክ ሽያጮች ላይ ሳንመሠረት እንኳን በመቀጠል እንችላለን" ያሉት ሬን የአሜሪካ ኩባንያዎች ያለፍቃድ ከሁዋዌ ጋር እንዳይሠሩ የሚያግደውን የጥቁር መዝገብ ያነሳል የሚል እምነት እንደሌላቸው ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡