ኮሮናቫይረስ፡ ደቡብ ኮርያ ለድመት እና ውሾች የኮቪድ-19 ምርመራ ልታደርግ ነው

ደቡብ ኮሪያ በዋና ከተማዋ ሶል የሚገኙ ውሾች እና ድመቶች የኮቪድ-19 ምልክት ካሳዩ ምርመራ እንደሚደረግላቸው የሶል ሜትሮፖሊታን አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከጥቂት ሳምንታት በፊት በኮቪድ-19 የተያዘች ድመት መገኘቷን ተከትሎ ነው።

ምልክቱን የሚያሳዩ የቤት እንሰሳት ብቻ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

በተጨማሪም ቫይረሱ ለያዘው ሰው የተጋለጡና ትኩሳት ወይንም ደግሞ የመተንፈስ ችግር የገጠማቸው ድመትና ውሾች ምርመራ እንደሚደረግላቸው ተገልጿል።

እነዚህ የቤት እንስሳት ተመርምረው ተህዋሲው እንዳለባቸው ከተረጋገጠ በቤት ውስጥ ራሳቸውን አግልለው እንዲቀመጡ ይደረጋል።

እንደ ዩንሃፕ የተሰኘ መገናኛ ብዙኀን ዘገባ ከሆነ የደቡብ ኮሪያ በሽታ መቆጣጣር ኃላፊ የሆኑት ፓርክ ዮ ሚ እነዚህ የቤት እንስሳት መንግሥት ወዳዘጋጃቸው ለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት አይጠበቅባቸውም።

ነገር ግን የእነዚህ እንስሳት ባለቤት በኮቪድ-19 ታምሞ ሆስፒታል ከገባ፣ በጠና ከታመመ ወይንም ደግሞ በእድሜ መግፋት ምክንያት ለመንከባከብ ካልቻለ የከተማ አስተዳደሩ ወደሚያስተዳድረው የለይቶ ማቆያ ይወሰዳሉ ተብሏል።

እስካሁን ድረስ የኮሮናቫይረስ ከቤት እንስሳት ወደ ሰው ስለመተላለፉ የተገኘ ማረጋገጫ የለም።

ኃላፊዋ አክለውም ነዋሪዎች "የቤት እንስሳቶቻቸውን በሚያንሸራሽሩበት ወቅት ከሰዎችም ሆነ ከሌሎች እንስሳት ቢያንስ ሁለት ሜትር እንዲያርቋቸው" አደራ ብለዋል።

ባለፈው ወር በአንድ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ የተገኘች ድመት በኮሮናቫይረስ መያዟ በምርመራ መረጋገጡን ዮንሃብ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የጤና ባለሙያዎች በሃይማኖት ተቋሙ ውስጥ የነበሩ እናትና ልጅ ቫይረሱን ወደ ድመቷ ማስተላለፋቸውን ጠርጥረዋል።

እናትና ልጅ በኮቪድ 19 መያዛቸው ተረጋግጧል።

ባለሙያዎች ድመትም ሆነ ውሻ ቫይረሱን ወደ ሰው የማስተላለፍ እድላቸው በጣም የጠበበ ነው ያሉ ሲሆን ድመቶች ግን እርስ በእርስ ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ይችላሉ ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ የቤት አንስሳት በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጦ ያውቃል።

ባለፈው ወር በሳንዲያጎ መካነ አንስሳት ሁለት ጎሬላዎች ይንከባከባቸው ከነበረ ግለሰብ የኮሮናቫይረስ ተይዘው ተገኝተዋል።

በኒውዮርክ ብሮንክስ መካነ አንስሳት ደግሞ ዝሆን እና ታይገር፣ በስፔን ባርሴሎና መካነ እንስሳት አንበሳ በኮሮና ተህዋሲ ተይዘዋል።