ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኩባ ኢኮኖሚዋን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ልታደርግ ነው
ኢንዱስትሪዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ብቻ በሚንቀሳቀሱባት ኩባ አንዳንድ ዘርፎች ከመንግሥት እጅ ወጥተው በግሉ ዘርፍ ለባለሀብቶች ክፍት ሊደረጉ ነው።
የሥራና ሠራተኞች ሚኒስትር ማርታ ኤሌና እንዳሉት አሁን የግል ባለሀብት ሊገባባቸው የሚችሉ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ከ127 ወደ 2000 እንዲሆኑ ተደርጓል።
ይህም ማለት ጥቂት ዘርፎች ብቻ ናቸው በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚቆዩት።
የኮሚኒስቷ አገር ኩባ ባለፉት ዓመታት ምጣኔ ሀብቷ ክፉኛ መጎዳቱ ይታወሳል። ይህም የሆነው አንድም በወረርሽኝ ምክንያት ሲሆን ሁለተኛው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በኩባ ላይ ጥሎት በነበረው ማዕቀብ ነው።
ባለፈው የአወሮፓውያኑ ዓመት ብቻ የኩባ ኢኮኖሚ 11% ቁልቁል ተንሸራቷል። ይህም በ30 ዓመት ውስጥ የከፋው ነው ተብሏል። ኩባዊያን ለኑሮ መሠረታዊ የሚባሉንት እንኳ ለመሸመት ተችግረዋል።
ሚኒስትሯ ማርታ 124 ኢንዱስትሪዎች ብቻ ናቸው ለግል ዘርፍ ክፍት የማይደረጉት ብለዋል። ሆኖም እነዚህ የትኞቹ እንደሆኑ ከመዘርዘር ተቆጥበዋል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ምናልባት እነዚህ በመንግሥት እጅ ብቻ ይቆያሉ የተባሉት ሚዲያ፣ ጤናና መከላከያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ይሆናሉ ሲል ግምቱን አስቀምጧል።
በኩባ በሺህ የሚቆጠሩ በግል ከተያዙ አነስተኛና ጥቃቅን እርሻዎች ሌላ በመንግሥት ያልተያዘው ዘርፍ በባለቤትነት የሚይዙት እንደ የነጋዴዎች ማኅበር፣ የእጅ ሙያ ባለቤቶች ማኅበር እንዲሁም የታክሲ አሽከርካሪዎች ማህበርና የመሳሰሉት ናቸው።
የአገሪቱ 40 ከመቶ የሚሆነው የግል ቢዝነስ ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ በመሆኑ ወረርሽኙን ተከትሎ ከፉኛ ተጎድቷል።
ላለፉት 60 ዓመታት በአሜሪካና በኩባ መካከል የነበረው ቅራኔ መሻሻል አሳይቶ የነበረው በአውሮፓውያኑ 2015 ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማና የኩባው ራውል ካስትሮ ግንኙነታቸውን ጤናማ ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ ነበር። ይህን ተከትሎ የአሜሪካ ዜጎች ኩባን እንዲጎበኙ፣ አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችም እንዲያብቡ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተፈጥረው ነበር።
ሆኖም ይህ የትራምፕ ግንኙነቱን የማሻሻል ጥረት በተተኪያቸው ዶናልድ ትራምፕ ውድቅ ተደርጓል። የትራምፕ ደጋፊ የሆኑ የኩባ አሜሪካዊያን የኦባማን ከራውል ካስትስሮ ጋር መገናኘት የኮሚኒስት አገሯን የመለማመጥ ያህል ነው ብለው ሲቃወሙ ነበር።
ትራምፕም የደጋፊዎቻቸውን ቅሬታ ሰምተው ኩባ ላይ ማእቀብ ጥለዋል።
አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በምርጫ ቅስቀቸው ወቅት አገራቸው ከኩባ ጋር ያላትን ግንኘኙነት ለማደስ እንደምትፈልግ መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን ነገር ግን ይህ አጀንዳ ምን ያህል ቅድሚያ የሚሰጡት ይሆናል የሚለው ግልጽ አይደለም።