ኢሰመኮ በረሃብ አድማ ላይ ናቸው የተባሉትን እነ አቶ ጃዋርን መጎብኘቱን ገለፀ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የረሃብ አድማ ላይ ናቸው የተባሉትን በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ እስረኞች መጎብኘቱን ዛሬ፣አርብ ባወጣው መግለጫ ላይ ገለፀ።

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙ እስረኞችን አስመልክቶ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ "የእስረኞቹ ጤንነትና ሕይወት የከፋ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ለታሳሪዎች ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የእስረኞችን ጠያቂዎች በማረሚያ ቤቱም ሆነ በፍርድ ቤቶች በአግባቡ ማስተናገድ ይገባል" ማለታቸውም ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

ኮሚሽኑ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እና በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማቆያ በመገኘት እስረኞቹን መጎብኘቱን የገለፀ ሲሆን ከእነ አቶ ጃዋር መሐመድ በተጨማሪም፣ የኮሎኔል ገመቹ አያና እና የአቶ ጥላሁን ያሚ አያያዝ ላይም ክትትል ማድረጉን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ከጥር 19 ጀምሮ በረሃብ አድማ ላይ እንደነበሩ የገለፀው ኮሚሽኑ፣ የረሃብ አድማው ዓላማ "መንግስት በሕዝብ እና በፓርቲያቸው ላይ እያደረሰ ያለውን አፈና እና የመብት ጥሰት ለመቃወም፣ የኮሎኔል ገመቹ አያናን አላግባብ የሆነ አያያዝ እና እንግልት እንዲቆም ለመጠየቅ እና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ እና እነሱን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ" መሆኑን ለኮሚሽኑ ማሳወቃቸው ተመልክቷል።

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በበኩሉ እነ አቶ ጃዋር ያነሷቸው አብዛኞቹ ጉዳዮች እንደማይመለከቱት መግለፁን በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።

እነ አቶ ጃዋርን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት የሚመጡ ሰዎች ላይ ወከባ እንደማይፈፀምም ማረሚያ ቤቱ ማስታወቁ ተገልጿል።

ከመካከላቸውም ሁለት እስረኞች የጤና ችግር ያለባቸው በመሆኑ በረሃብ አድማው ምክንያት የጤና እክል እንዳይገጥማቸው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን መመልከቱን ኮሚሽኑ ገልጿል።

አቶ ጃዋር መሃመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሃምዛ አዳነ እና አቶ ሸምሰዲ ጠሃ በትናንትናው እለት በረሃብ አድማው በመዳከማቸው ችሎት ፊት ሃሳባቸውን ማስረዳት እንደተሳናቸው ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ መሐመድ ጅማ ለቢቢሲ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

"ሰውነታቸው በጣም ስለተዳከመ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። እነሱ ብዙ መናገር ስላልቻሉ እኛ ሃሳባቸውን አስረድተናል።" ብለዋል።

ተከሳሾቹም እንዲሁ "በጣም ተዳክመን፣ ራሳችንን ስተን የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገን ከሆነ እኛ በመረጥነው ሃኪም ብቻ የህክምና ርዳታ ይደረግልን' ሲሉ ፍርድ ቤቱን እንደጠየቁም ጠበቃቸቸው አስረድተዋል።

ከእነ አቶ ጃዋር በበተጨማሪም ኮሚሽኑ የኮሎኔል ገመቹ አያናን እና ጥላሁን ያሚን ደህንንት ማጣራቱንም አስታውቋል።

"ሁለቱም ታሳሪዎች በመልካም ደህንነት ላይ ይገኛሉ" ያለው ኮሚሽኑ አካላዊ ጥቃትም እንዳልደረሰባቸው ማረጋገጡን አስታውቋል።

አቶ ጥላሁን ዋሚ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከማረሚያ ቤት ተቀርጾ በተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል ጋር በተያያዘ ደህንነቱ አደጋ ላይ ወድቋል ተብሎ በስፋት ሲወራ ነበር።

ጥላሁን ዋሚ በማሕበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውን ቪዲዮ ተከትሎ ከማቆያ ቤቱ ቅጥር ግቢ እንዳይወጣ ከመደረጉ በስተቀር በቂሊንጦ ጊዜያዊ ማቆያ እያለ ድብደባም ሆነ ሌላ አይነት የመብት ጥሰት እንዳልተፈፀመበት ለኮሚሽኑ ማስረዳቱ ተገልጿል።