በአውስትራሊያዊቷ ፀሐፊ የተፃፈው የፈይሳ ሌሊሳ ታሪክ

ፈይሳ ሌሊሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ኧ ታይም ቱ ቢ ቦርን' - የፈይሳ ሌሊሳ ታሪክን የሚዳስስ መፅሐፍ ነው።

"ለተቃውሞው ያለኝን ድጋፍ ለማሳየት ለየት ያለ መንገድ መርጫለሁ። በ2016 [በፈረንጆቹ] የተካሄደው የሪዮ ኦለምፒክ ላይ እጄን አጣምሬ ወደ ላይ ማንሳቴ ምን ያክል ትርጉም እንዳለው ሳስብ አሁንም ድረስ እገረማለሁ።"

ዓለም በጉጉት ሲመለከተው በነበረው የሪዮ ዲ ጄኔሪዮ ኦለምፒክ መድረክ ላይ ፈይሳ አንድ ያልተጠበቀ ድርጊት ፈፀመ። ይህ ጉዳይ ከሃገር ቤት አልፎ የዓለም መነጋገሪያ ለመሆን በቃ።

በወቅቱ ኢትዮጵያን ያስተዳድር የነበረው መንግሥት ከሃገር ውስጥና ከውጭ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። በዚህ ተቃውሞ ላይ የኦሮሞ ወጣቶች ሚና ጎልቶ የወጣ እንደነበር የማይካድ ነው።

ሁለት እጆችን ወደላይ ከፍ አድርጎ ማጣመር ደግሞ የተቃውሞው አርማ ነበር።

ሌሊሳም ያደረገው ይህንን ነው። በማራቶን ውድድር ተሳትፎውን ጨርሶ የመጨረሻው መስመር ላይ ሲደርስ ሁለቱን እጆቹን በማጣመር ተቃውሞውን በይፋ ተቀላቀለ። ዓለምም ጉድ አለ።

አውስትራሊያዊቷ ፀሐፊ ስቴፋኒ ይህን ተከትላ በፈይሳ ሕይወት ዙሪያ አንድ መፅሐፍ ለመፃፍ ቆርጣ ተነሳች። ያሰበቸውም ተሳክቶ 'ኧ ታይም ቱ ቢ ቦርን - ዘ ስቶሪ ኦፍ ፈይሳ ሌሊሳ' የተሰኘ ታሪክ አሳትማለች።

ዘንድሮ በታተመው በዚህ መፅሐፍ የመጀመሪያ ክፍል ፈይሳ ከብሪታኒያዊው ሞ ፋራህ ስለተበረከተለት ስጦታ ይዘክራል።

"ለኔ በጣም ጎልተው ከሚወጡ ነገሮች አንዱ ይሄ ነው" ይላል ፈይሳ ከሩጫው በኋላ ስለተፈጠረው ነገር ሲያወራ።

"ከ ሞ ፋራህ በጣም ውድ ስጦታ ተሰጠኝ። ተቃውሞዬን ከግምት በማስገባት ልዩ የሆነ ጫማ አበረከተልኝ።"

"ፈይሳ፤ እኔም በአንድ ወቅት እንዳንተ ነበርኩኝ። የምጫማው ጫማ አልነበረኝም" ሲል ሞ ፋራህ ነገረኝ ይላል ፈይሳ። ፈይሳ ሞ ፋራህ ጫማውን ሲያበረክትልኝ ዓይሞቹ እምባ ቀሯቸው ነበር ይላል።

"እኔም እንዳንተ ፈተና የበዛባት ሃገር ነው ትቼ የመጣሁት" ሲል እንደነገረው ፈይሳ በመፅሐፉ አስነብቧል።

መፅሐፉ ስለ ፈይሳ እጅ ማጣመር ብቻ የሚያወራ አይደለም። ስለ ኦሮሞ ተቃውሞ ጭምር እንጂ። የፈይሳ የተጣመሩ እጆች ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ተቃውሞ ለዓለም ተናግረዋል።

የመፅሐፉ ተያቢ

ምንም እንኳ መፅሐፉን የፃፈችው አውስትራሊያዊቷ ስቴጋል ትሁን እንጂ የሚተርከው ፈይሳ ነው።

የፈይሳ ትዝታዎች በጉልህ የተቀመጡ ናቸው። ፀሐፊዋ ፈይሳ የት እንዳደገ፤ ያደገበትን ሥፍራ መልክዓ ምድር፤ ቤተሰቦቹን፤ ሲያድግ ያስተውለው የነበረው ኢ-ፍትሐዊነትን አጥንታለች።

ፈይሳን ካደገበት ሥፍራ ጋር ምን ያህል የተቆራኘ ማንነት እንዳለው መፅሐፉ ይተነትናል።

አውስትራሊያዊቷ ፀሐፊና አስተማሪ ዶክተር ስቴፋኒ ስቴጋል አዲስ አበባ የመጣችው የበጎ ሥራ ተግባራት ላይ ለመሠማራት ነው።

ታድያ ሸገር ሳለች ፈይሳን እጁን አጣምሮ ሃገር አጀብ ሲያሰኝ፣ ዓለምን ሲያነጋግር ተመለከተች። ይሄኔ ነው የፈይሳ ሕይወት ቀልቧን የገዛው።

"ኢትዮጵያ ጥንታዊና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነች ሃገር ናት። ምንም እንኳ ስሟ ከድህነት ጋር ይያያዝ እንጂ በረዥም ርቀት ሯጮቿም ትታወቃለች። ይህ ነው ሁሌም እንድገረም የሚያደርገኝ" ትላለች ዶ/ር ስቴጋል።

ዶ/ር ስቴጋል ወደ ኢትዮጵያ ያቀናችው በፈረንጆቹ ነሃሴ 2016 ነበር። ስትመጣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማገልገል ነበር። አዲስ አበባ ከመግባቷ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከተማዋ በተቃውሞ ታምሳ ነበር።

"ልክ እንደ መጣሁ ሰዉን መታዘብ ጀመርኩ። የአኗኗር ዘይቤያቸውን እና ውስጣቸውን ያለውን ቁጣ ማየት ችዬ ነበር" የምትለው ፀሐፊዋ የፈይሳን ሕይወት ማጥናት ተያያዘች።

ከፈይሳ ፈቃድ ካገኘች በኋላ ነው ወደ ሥራዋ የገባችው። ከዚያ በኋላ ያለው ታሪክ በመፅሐፉ ላይ ቁልጭ ብሎ ታትሟል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ያሳለፍኩት፣ ከፈይሳ ጋር የነበረኝ ግንኙነት፣ ከሌሎች ወዳጆቼ ጋር የነበረኝ ቆይታ እንደሁም ቃል ምልልስ ያደርግኳቸው ሰዎች ናቸው ይህን መፅሐፍ እንዳገባድደው የረዱኝ" ትላለች ፀሐፊዋ።

ዶ/ር ስቴጋል ለፈይሳ ያላት አድናቆት እጅግ ለየት ያለ ነው። እሱም ታሪኩን ሳይሸሽግና ሳይነፍግ ሙሉ በሙሉ አጫውቷታል። የሱን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክን ጭምር።

ነሃሴ - 2016 - ሪዮ

ፀሐፊዋ መፅሐፉን የምትጀምረው ከታች በተጠቀሰው የፈይሳ ንግግር ነው።

"የሪዮ ኦለምፒክ ላይ ስሳተፍ ልቤ ሙሉ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ወንዶች፣ አብዛኛዎቹ በኔ ዕድሜ ያሉ በመንግሥት እጅ በጭካኔ ተገድለዋል። ይሄን እያሰብኩ ነው የሮጥኩት። የቅርብ ጓደኞቼ ትዝታ፣ ቤተሰቤ፣ ዘመዶቼ ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ ተገድለዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ታሥረዋል፣ ታፍነው ተወስደዋል፣ ሰብዓዊ ክብራቸው ተገፏል። ይህንን ኢ-ፍትሐዊነት በውስጤ አድርጌ ነበር ስሮጥ የነበረው። ይህን ጭካኔ እኔም አይቼዋለሁ፤ ስሰማው የኖርኩትም ታሪክ ነው። ለዚህ ነው በሪዮ ኦለምፒክ መድረክ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞዬን ማሰማት የመረጥኩት"

ምንም እንኳ የወንዶች ማራቶን ውድድርን ኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ ቢያሸንፈውም ፈይሳ ሌሊሳ ሁለተኛ ከመውጣት ባለፈ ታሪክ መሥራት ችሏል።

የፈይሳ ሚስት ኢፍቱ ሙሊሳ በወቅቱ አዲስ አበባ ነበረች። ሩጫውን በቴሌቪዥን መስኮት ስትከታተልም ነበር።

"በጣም ፈርቼ ነበር። ነገር ግን ብዙ አልተገረምኩም። ምክንያቱም ውስጡ የነበረውን ቁጣ አውቅ ነበር" ትላለች ኢፍቱ።

ፈይሳ ልክ እንደሌሎቹ ተቃዋሚዎች መንግሥት በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ጭቆና ይጠየፍ ነበር።

በ1982 ዓመተ ምሕረት ቱሉ ቡልቱማ በተሰኘች ከተማ የተወለደው ፈይሳ የቤተሰቦቹን ከብት በመጠበቅ ነበር ልጅነቱን ያሳለፈው።

የልጅነት ምኞቱ ሲያድርግ ወታደር መሆን ነበር። ነገር ግን በረዥም ርቀት ሩጫ ኮከቦቹ አበበ ቢቂላና በኃይሌ ገብረስላሴ ታሪክም ይመሰጥ ነበር።

ፈይሳ ስለ ወንዱ አያቱ ተናግሮ አይጠግብም። አያቱ የሚነግሩትን ታሪክ እየሰማ ነበር ያደገው። በልጅነቱ ከሚያዘውትራቸው ጨዋታዎች አንዱ የፈረስ ግልቢያ ነበር።

ወደ ትምህርት ቤት በሩጫ መሄድ፣ ቅዳሜ ገበያ ሄዶ ዶሮና በግ ለመሸጥ የሚያቋርጣቸው አረንጓዴ መስኮች፣ ማራኪው መልክዓ ምድር፣ ማሕበረሰባዊ እሴቶች በፈይሳ ትዝታ ማሕደር ውስጥ ታትመው የተቀመጡ ናቸው።

ይህን የፈይሳን መፅሐፍ የሚያነብ ሰው ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ ማወቁም የማይቀር ነው። የኦሮሞ ሕዝብ ባሕል፣ እምነትና ቋንቋ ይዳሰሱበታል መፅሐፉ።

ፀሐፊዋ የፈይሳን አስተሳሰብ ለመረደት ብዙ ጊዜ አብራው ቁጭ ብላ ወግ ትጠርቅ እንደነበር፤ አንዳንዴ ክርክር ሁላ ውስጥ እንደሚገበ ኡ ትናገራለች።

የቀረውን ለአንባቢው መተው ሳያዋጣ አይቀርም። ነገር ግን መፅሐፉ ከፈይሳ ታሪክ እጆችና ከሕይወቱ በዘለለ በርካታ እሴቶች የታጨቁበት እንደሆነ ሹክ ማለት ያሻል።

ፈይሳን ለተቃውሞ እጆቹን ለምን አነሳ? ከትውልድ መንደሩ ወደ አዲስ አበባ ያደረገው ጉዞ ምን ይመስል ነበር? ከዓለም አቀፍ ውድድሮች ያገኘው ነገር ምንድነው? ለሁለት ዓመታት በስደት መኖር ምን ይመስላል? ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ለምን ወሰነ? ሲመለስ ምን ገጠመው? መፅሐፉ ከሚመልሳቸው ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

መፅሐፉ ወደ ኢትዮጵያ ቋንቋዎቹ መቼ ሊተረጎም ይችላል የሚለው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም።

ፀሐፊዋ በኋላኛው የመፅሐፉ ገፆች ከጥቅምት 2018 [በፈረንጆቹ] ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ ክስተቶችንና ፈይሳ ላይ የፈጠሩትን ተፅዕኖ ትዳስሳለች።

ነገር ግን የመፅሐፉ ኦፊሴላዊ መጠናቀቂያ ክፍል ፈይሳ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት መፅሐፉ የተጠናቀቀው ከአንድ ዓመት በፊት ስለሆነ ነው ትላለች።