የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ለተመረጡ የውጭ ዜጎች ዜግነት ልታድል ነው

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በአገሯ ውስጥ ገብተው ለሚሰሩና ለሚማሩ አንዳንድ የውጭ ዜጎች የኢምሬትስ ዜግነትን እሸልማለሁ ብላለች፡፡

ዜግነት የሚሰጣቸው ግን ባለ ልዩ ተሰጥኦ ለሆኑት ብቻ ነው፡፡

ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ‹አዲስ እሴት የሚጨምሩና ልዩ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን› ዜግነት ጭምር እንሰጣቸዋለን ብለዋል የዱባዩ ገዥ ሼክ መሐመድ ቢን ራሺድ አል መክቱም፡፡

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስት ምክትል ፕሬዝዳንትም ጭምር የሆኑት የዱባይ ገዥ ሼክ አልመክቱብ እንዳብራሩት ዜግነት የሚሰጣቸው ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሐኪሞች፣ መሐንዲሶች፣ አርቲስቶች፣ ባለሐብቶችና የፈጠራ ባለቤቶችም ጭምር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ዜግነቱ የሚሰጠውም ለባለ ልዩ ተስጥኦዎች ብቻ ሳይሆን ከነቤተሰባቸው ጭምር ነው ብለዋል አልመክቱብ፡፡

ሼክ መሐመድ ቢን ራሺድ አል መክቱብ በሰጡት ይህ ትልቅ ዕድል ውስጥ በአነስተኛ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ዕድሉን የመጠቀም ዕድላቸው እጅግ አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡

ይህ ዜግነትን የመስጠቱ ሐሳብ የመጣው ኢምሬትስ በእድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰች በመሆኗ ለእድገቷ አዲስ እሴት የሚጨምሩ ሰዎችን ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል፡፡

ዜግነቱን ለማግኘት የማመልከቻ ሂደት የለውም፡፡

እጩዎቹ የውጭ ዜጎቹ በኢምሬትስ ባለሥልጣናት ነው የሚጠቆሙት ዜግነቱን የሚሸለሙት፡፡ ከዚያ የኢምሬትስ ካቢኔ ዜግነቱን በማጽደቁ ሂደት ድምጽ ይሰጥበታል፡፡

ይህ አዲስ ዘዴ የውጭ ኢንቨስተሮችና የባለ ልዩ ሙያ ባለቤቶች ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጥብቅ እንዲሆንና አገሪቱን እንደ አገራቸው እንዲያስቡ የሚያደርግ ይሆናል ተብሏል፡፡

ይህ እርምጃ የመጣው የነዳጅ ምርት በተቀዛቀዘበትና ብዙ የውጭ ዜጎች በሥራ እጦት አገሪቱን ለቀው በወጡበት ወቅት ነው ብሏል አንድ የአገሪቱ ጋዜጣ፡፡

የቢቢሲ የአረብ ጉዳዮች አርታኢ ሰባስቲያን አሸር እንደሚለው የገልፍ አገሮች የፋይናንስና የቱሪዝም ማዕከል መሆን የሚወሰነው በውጭ አገራት ዜጎች ነው፡፡

የነዚህ አገራት የሥራ ኃይል 90 ከመቶ በውጭ ዜጎች ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ነዋሪዎችም ቢሆኑ በብዛት የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡

ብዙዎቹ የውጭ ዜጎች ለዓመታት የሚታደስ የሥራ ቪዛ ይዘው እንዲቆዩ ይገደዳሉ፡፡

ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኙ የጉልበት ሠራተኞችም ለኢምሬትስ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡

በተለይም ለግንባታ ዘርፉ የሰው ኃይል በማቅረብ ትልቁን ሚና ይወስዳሉ፡፡ ብዙዎቹ ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኙ የውጭ ሰራተኞች የሚያገኙትን ገቢ ወደ አገር ቤት የሚልኩ ናቸው፡፡ ሆኖም በአገሪቱ በንቀት የሚታዩ ናቸው፡፡

ብዙዎቹ በኢምሬትስ የሚገኙ ሰራተኞች የዕድሜ እኩሌታቸውን እንኳ በዚያ ቢያሳልፉም ቋሚ የነዋሪነት ፈቃድም ሆነ ዜግነት የማግኘት መንገዶች ጠባብ ሆነው ቆይተዋል፡፡

ያም ሆኖ ዝቅተኛ ገቢ የሚያስገኙ የጉልበት ሥራዎችን የሚሰሩ የውጭ ዜጎች በአመዛኙ በኢምሬትስም ሆነ በሌሎች የጎልፍ አገሮች ዝቅ ተደርገው ነው የሚታዩት፡፡

ይህ ዝቅተኛ ዜጎችን ያገለለው አዲሱ የዜግነት እደላ ዕድል ከፍ ባሉ ሙያዎች ላይ ላሉና የውጭ አገር ዜጋ ሆነው መዋእለ ነዋያቸውን በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ለሚያፈሱ ብቻ የታቀደ ይመስላል፡፡

ከ2 ዓመት በፊት ሼክ መሐመድ አልመክቱብ ለባለሐብቶች፣ ለሐኪሞችና ሳይንቲስቶች ወርቃማ ካርድ የሚል ቪዛ መስጠት መጀመራቸው ይታወሳል፡፡

ይህም የተመረጡ የውጭ ዜጎች ለ10 ዓመት የሚያገለግል ቪዛን እንዲያገኙ የሚያደርግ ነበር፡፡

ይህ ወርቃማ ቪዛ ከፍተኛ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎችም የሚሰጥ ሁኔታ ነበር፡፡

አሁን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዜግነትን ለማግኘት የሚሻ ባለሐብት ከፍ ያለ ንብረትና ኩባንያ በዚያች አገር ሊኖረው ይገባል፡፡

ሐኪሞች ደግሞ በአንድ ከፍተኛ ፍላጎት ባለው የጤና ዘርፍ የሰለጠኑ (ስፔሻላይዜሽን ያላቸው) ሊሆን ይገባል፡፡

አዲስ ሐሳብ ፈጣሪዎች የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት ፈቃድ ያገኙ መሆን አለባቸው፡፡

እነዚህ አዲስ ዜግነት የሚሰጣቸው የውጭ ዜጎች የአገሪቱ የዌልፌር ሲስተም ተጠቃሚ ይሆናሉ ወይ የሚለው ለጊዜው አልተመለሰም፡፡

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ አንድ ሚሊዮን ተኩል ለሚሆኑ ዜጎቿ ነጻ ትምህርት፣ የጤና ሽፋን፣ የቤት ብድርና ሌሎች ከፍ ያሉ ጥቅማ ጥቅሞችን ትሰጣለች፡፡

ሆኖም አዲስ ዜግነት የሚያገኙ የውጭ ዜጎች እነዚህን ሁሉ ጥቅማ ጥቅሞች ያገኛሉ ወይ የሚለው በግልጽ አልተቀመጠም፡፡

በገልፍ የአረብ አገራት ዜግነት መስጠት እምብዛምም የተለመደ አይደለም፡፡

ዜግነት ከተሰጠም የኢምሬት ዜግነት ላለው ሰው ሚስት ወይም ሚስቶች ወይም ደግሞ ለኢምሬት ዜግነት ካለው አባት የተወለዱ ልጆች ብቻ ነው፡፡

የውጭ ዜጋ አግብታ የወለደች የኢምሬት ዜጋ እናት የሚወለዱ ልጆቿ በቀጥታ ዜግነት አያገኙም፡፡