ምዕራባውያኑ የትግራዩን ግጭት ተከትሎ ያላቸውን ስጋት ዳግም ገለጹ

የአሜሪካ ዲፕሎማቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት እና አውሮፓ ሕብረት ተወካዮች በትግራይ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ስጋት ገለጹ፡፡

ስጋታቸውን ከገለጹት መካከል አራት የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደሮች ይገኙበታል።

አራቱ የቀድሞ አምባሳደሮች ጽኑ ስጋታቸውን ያንጸባረቁት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ነው፡፡ አምባሳደሮቹ በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት እንዳሳሰባቸው ለሪፖርተር ጋዜጣ በላኩት ይፋ ደብዳቤ አስታውቀዋል።

አራቱ የቀድሞ አምባሳደሮች በትግራይ የተከሰተውን ግጭት በአጽንኦት መከታተላቸውን እና ግጭቱን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸው እጅጉን እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከ60ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ስለመሸሻቸው፣ ወደ 2.2 ሚሊዮን የሚገመት ሕዝብ በክልሉ ውስጥ መፈናቀሉን እና 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግሥት ድርጅት አሐዞች ይጠቁማሉ።

የአገሪቱ መንግሥት በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 2.5 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን እና ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እንዲሁም መድኃኒት እያቀረበ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል።

ደብዳቤውን የጻፉት አራቱ የቀድሞ አምባሳደሮች አምባሳደር ዴቪድ ሺን፣ ኡሬሊያ ብራዜለ፣ ቪኪ ሃድልስተን እና ፓርቲሺያ ሃስላች እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር ከ1996 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

አራቱ የቀድሞ አምባሳደሮች ለጠቅላይ ሚንስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፤ በአገሪቱ ዘርን መሠረት ያደረገ ውጥረት እያየለ መምጣቱ፣ የጥላቻ ንግግር መበራከቱ እንዲሁም ብሔርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት እዛም እዚህም መስፋፋቱ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የአገልግሎት ጊዜያቸውን እያጠናቀቁ ያሉት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ራይነር ትናንት በኤምባሲያቸው ጋዜጠኞችን ጠርተው አነጋግረዋል።

አምባሳደሩ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ እየወጡ ባሉ ሪፖርቶች ዙሪያ በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ተሰናባቹ አምባሳደር ግጭቱን ተከትሎ ተፈጽመዋል ስለተባሉ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥት በትግራይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ሪፖርቶች እየደረሱት መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

አምባሳደሩ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በበቂ ሁኔታ እርዳታ እየደረሳቸው ስላልሆነ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ተቋማት ድጋፋቸውን በአስቸኳይ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮችን ተቀብለው አነጋግረዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በትግራይ ክልል እየተደረገ ስለሚገኘው የሰብዓዊ ድጋፍ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስተባባሪ ለሆኑትን ካትሪን ሶዚን (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋቸዋል።

ካትሪን ሶዚ (ዶ/ር)፤ ክስተቱን ተከትሎ መንግሥት እያደረገ ያለው ምላሽ የሚደነቅ እንደሆነ፤ ከሁኔታው ጋር ተያይዞ የተሰራጩትን የተዛቡ መረጃዎችን በድርጅታቸው በኩል ለማጣራት እንደሚንቀሳቀሱ ስለመናገራቸው የሰላም ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል።

በተመሳሳይ መልኩ የፋይናንስ ሚንስትሩ አህመድ ሺዴ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ተወካይን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱ ላይ አህመድ ሺዴ በትግራይ ያለውን መልሶ ግንባታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ በማስመልከት መንግሥት እያከናወነ ስላለው ተግባር ማስረዳታቸውን ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።

ኤሪክ ሃቤርስ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን በተመለከተ ለነበራቸው ስጋት የፋይናንስ ሚንስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል ብሏል የፋይናንስ ሚኒስቴር።

አህመድ ሺዴ በውይይቱ ወቅት በትግራይ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን እና ይህም የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በሚገኘው ሠራዊቱ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት ተሰንዝሯል በሚል ነበር ወታደራዊ ዘመቻ የከፈተው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሠራዊቱ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበርና "ወንጀለኛውን ቡድን" ለሕግ ለማቅረብ የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፌደራሉ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ያሳወቁትን የህወሓት አመራሮችን ለመያዝ አሰሳ እያካሄደ ይገኛል።

እስካሁንም በርካቶች መያዛቸውንና መገደላቸው የአገሪቱ ሠራዊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።