ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይደን እና ፑቲን በስልክ ተወያዩ
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በነበራቸው የመጀመሪያ የስልክ ጥሪ በምርጫ ላይ ተጽእኖ መፍጠር ዙሪያ ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጡ።
ሁለቱ መሪዎች በነበራቸው የመጀመሪያው የስልክ ውይይት በአሁኑ ወቅት በሩሲያ እየተካሄደ ስላለው መንግሥታዊ ተቃውሞ እና ስለ አሜሪካ-ሩሲያ ኒውክለር ስምምነት የተነሱ አጀንዳዎች እንደነበሩ የሩሲያ መንግሥት መግለጫ አመልክቷል።
በመግለጫው እንደተገለጸው ሁለቱ መሪዎች ወደፊት ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል ስለመስማማታቸው ተገልጿል።
ጆ ባይደን ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ያገለገሉበት የኦባማ አስተዳድር፤ ክሬምሊን ክሬሚያን በኃይል ስትይዝ፣ ምስራቅ ዩክሬንን ስትወር እና በሶሪያ ጉዳይ ጣልቃ ስትገባ ማስቆም ባለመቻሉ ሲተች ቆይቷል።
ሁለቱ መሪዎች ምን ተነጋገሩ?
"ፕሬዝደንት ባይደን የአሜሪካን ብሔራዊ ፍላጎት እንዲሁም ከሩሲያ ጋር ያላትን ግነኙነት ሊጎዳ በሚችል ነገር ላይ አስተዳደራቸው ጠንካራ አጸፋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቀዋል" ብሏል የባይደን አስተዳደር የሁለቱ አገራት መሪዎች ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ።
ውይይቱን በማስመልከት የሩሲያ ባለስልጣናት በበኩላቸው "ሩሲያ እና አሜሪካ ግነኙነታቸውን ማሻሻላቸው የሁለቱም አገራት ብሔራዊ ጥቅም የመከበር ፍላጎትን ያሳካል፤ ሁለቱ መሪዎች ግነኙነትን አሻሽሎ ለማስቀጠል እንዲሁም ለዓለም ደህንነት እና መረጋጋት ያላቸው ልዩ ኃላፊነት ላይ ከመግባባት ደርሰዋል" ይላል።
በአጠቃላይ በሩሲያ እና አሜሪካ መሪዎች መካከል የነበረው የስልክ ውይይት "ግለጽ" ነበር ይላል የክሬምሊን መግለጫ።
ሁለቱ አገራት በጦር ክምችታቸው ውስጥ በሚኖራቸው ሚሳኤል እና ሚሳኤል ማስተኮሻ ብዛት ላይ በኦባማ ዘመን ተደርሶ የነበረውን ስምምነት ዳግም ለማደስ መስማማታቸውም ተጠቅሷል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ይህን ስምምነት ለማሰቀጠል ፍላጎት አልነበራቸውም።
ባይደን ከክሬምሊን ጋር የተወያየቱ የአሜሪካ ሴኔት የአንቶኒ ብሊንከን የውጪ ጉዳይ ሚንስትርነት ሹመትን ባጸደቀበት ቀን ነው።
አንቶኒ ብሊንከን ማይክ ፖምፔዮን እንዲተኩ በ78 ድጋፍ፣ በ22 ተቃውሞ ሹመታቸው ጸድቆላቸዋል።
ባይደን ከሩሲያው መሪ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ በዋይት ሃውስ በመገኘት በአሜሪካ የአስተዳደር ስርዓት ውስጥ የዘር መድሎ ያስቀራሉ ያሏቸውን ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን የፍትሕ ቢሮው የግል ኩባንያዎች የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን እንዲያስተዳድሩ የገባውን ውል እንዲሻሽል ትዕዛዝ አስተላለፈዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ የኮሮናቫይረስ ሁለተኛ ዙር ክትባት ወስደዋል። ካማላ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በትራምፕ አስተዳደር ሥር ሊመረት የሚችል የኮቪድ ክትባት ውጤታማነት ላይ በሰጡት አስተያየት ተተችተው ነበር።
ካማላ ሃሪስ የወሰዱት ሞደርና ሰራሹ ክትባት በትራምፕ አስተዳደር ለሕዝብ እንዲሰጥ ፍቃድ ያገኘ ክትባት ነው።