"የባይደን ሹመት ለአሜሪካ ወደፊት መራመድ ነው"-ቦሪስ ጆንሰን

የፎቶው ባለመብት, NUMBER 10
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ለመጀመሪያ ጊዜ ለአቻቸው አሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደወሉ።
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሐሙስ ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልክ ደውለው ሁለቱ አገራት በጋራ ሊያከናውኗቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች እና ስለሚኖራቸው ትብብር አውርተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን በትዊተር ገጻቸው እንዳስታወቁት፣ በእንግሊዝ እና አሜሪካ መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት ለማስቀጠል በተስፋ እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሐሙስ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ ካማላ ሐሪስ ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚንስትር ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ተወያዩ
ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የባይደን ሹመት ለአሜሪካ "ወደፊት መራመድ" ነው ብለውታል። በዶናልድ ትራምፕ ዘመን አሜሪካ ራሷን አግልላባቸው የነበሩ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ እና የዓለም ጤና ድርጅት የመሳሰሉትን አሜሪካ ዳግም እንድትቀላቀል ፕሬዝዳንት ባይደን መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ በአድናቆት ተቀብለዋል።
የዳውኒንግ ስትሪት ቃል አቀባይ እንደገለጹት ፕሬዝዳንት ባይደን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ቀድመው የወሰዱት ርምጃ እና በ2050 (እአአ) የአየር ልቀትን ዜሮ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ያደረጉትን ጥረት ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ማድነቃቸውን ገልጿል።
ቃል አቀባዩ አክለውም "መሪዎቹ የሁለቱ አገራትን የቆየ የጸጥታ እና የመከላከያ ትብብር ለማሳደግና በሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ላይ ያላቸውን አጋርነት ለማሳደግ ተስማምተዋል" ያሉ ሲሆን የሁለቱ አገራት የጋራ እሴት የሆኑት ሰብዓዊ መብትን መጠበቅ እና ዲሞክራሲን ማጎልበት ላይ በጋራ እንደሚሰሩ መሪዎቹ መነጋገራቸውንም ቃል አቀባዩ ጨምሮ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ መሪዎች በነጻ ንግድ ስምምነት ዙሪያ ያለውን አዋጭነትም አንስተዋል ተብሏል።












