ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማዕድን ጉድጓድ ውስጥ የታፈኑትን ቻይናውያን ለማውጣት ሁለት ሳምንት ያስፈልጋል ተባለ
የቻይና ነፍስ አድን ሰራተኞች በመሬት ውስጥ 100 ሜትሮች ውስጥ ተቀብረው የሚገኙትን የማዕድን ሰራተኞች ሕይወት ለማትረፍ ተጨማሪ ሁለት ሳምንት እንደሚያስፈልጋቸው ገለፁ።
የማዕድን ሰራተኞቹ በጉድጓዱ ውስጥ ታግተው የቀሩት ከአስር ቀን በፊት በሥራ ላይ እያሉ በደረሰ ፍንዳታ ነው።
በሁሻን የወርቅ ማዕድን ጉድጓድ ውስጥ ተቀብረው ከሚገኙ ሰራተኞች መካከል ባለሥልጣናት 11 ሰራተኞችን ማናገር የቻሉ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን አንድ ግለሰብ መሞቱ ተዘግቧል።
የነፍስ አድን ሰራተኞቹ በጉድጓዱ ውስጥ የተቀበሩት ሰዎች ምግብ እና መድሃኒት የሚያገኙበትን አነስተኛ ቀዳዳ ቆፍረዋል።
የማዕድን ጉድጓዱ መግቢያ የተዘጋው ምክንያቱ ባልታወቀ ፍንዳታ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ለማዕድን ቆፋሪዎቹ በተቆፈረው ጉድጓድ በኩል ምግብና መልዕክቶች እየተላከ ቢሆንም እጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል የሚለው ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
እነዚህ የማዕድን ቆፋሪዎች በአሁኑ ሰዓት ከባለሥልጣናቱ ጋር እየተነጋገሩ ሲሆን፣ ከእነርሱ በታች 100 ሜትር ርቆ ብቻውን ያለ ሌላ ባልደረባቸውን አግኝተው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ግንኙነት መቋጡን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት 10 የማዕድን ቆፋሪዎች ከመሬት በታች 600 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። ከነፍስ አድን ሰራተኞች ጋርም በየጊዜው ይገናኛሉ።
በቻይና የማዕድን አደጋዎች የተለመዱ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ በደንብ ባልተተገበሩ የደህንነት ደንቦች ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው፡፡
በምስራቅ ቻይና ሻንዶንግ አውራጃ በያንታይ አቅራቢያ በሚገኘው ሁሻን የማዕድን ማውጫ ጣቢያ ላይ በደረሰው ፍንዳታ የማዕድን ማውጫውን መውጫ እና የግንኙነት ሥርዓት የጎዳ ሲሆን ሰዎቹን ለማትረፍ ርብርብ እየተደረገ ነው።
በቻይና የማዕድን አደጋዎች ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት የደህንነት ደንቦች በአግባቡ ካለመተግበር ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡
ባለፈው ዓመት ታህሳስ በድንጋይ ከሰል ማዕድን ማውጫ ካርቦን ሞኖክሳይድ አፈትልኮ 23 የማዕድን ሠራተኞች ሞተዋል፡፡
በመስከረም ወር በቾንግኪንግ ዳርቻ በሚገኝ ሌላ የማዕድን ማውጫ ስፍራ 16 ሠራተኞች ሕይወታቸው አልፏል፡፡
በጎርጎሮሳዊያኑ ታህሳስ 2019 በደቡብ ምዕራብ ቻይና በጊዡ ግዛት በከሰል ማዕድን ማውጫ ስፍራ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 14 ሰዎች ሞተዋል፡፡