ደቡብ አፍሪካና የዘር መድልዎ

እአአ በ2017 ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተከሰተ ነው። ግለን ሲንማን የተባለ መምህር ሥራ ሲያመለክት የቀረበለት ሰነድ ላይ "አፍሪካዊ" የሚለው ሰንጠረዥ ውስጥ ራሱን አስቀመጠ።

መምህሩ ከሦስት ወራት በፊት በማጭበርበር ተከሷል።

ግለን የተወለደው ከጥቁርና ነጭ ቤተሰብ ነው። የተመሠረተበት ክስ ቢነሳለትም፤ በአገሪቱ ያለው የዘር ክፍፍል ላይ ጥያቄ ያጫረ ክስተት ነው።

አፓርታይድ የዘር ልዩነትን መሠረት ያደረገ መድልዎን አስፋፍቷል። በ1950ዎቹ የወጣ ፖሊሲ ነጭ፣ አፍሪካዊ፣ ክልስ እና ሕንዳዊ በሚል አገሪቱን ለአራት ከፍሏል።

በ1991 ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሲመረጥ ይህ ፖሊሲ ቢሻርም ዘርን መሠረት ያደረገ ክፍፍል አሁንም ተወግዷል ማለት አይቻልም።

መንግሥት የምጣኔ ሀብት ልዩነትን ሲቃኝ ይህንን ክፍፍል ተመርኩዞ ነው።

ግለን 2010 ላይ ዘርን መሠረት ያደረገ ክፍፍል መኖር የለበትም ብለው ማኅበር ካቋቋሙ አንዱ ነው።

"በዘር ሰዎችን የሚከፋፍለው ፓሊሲ ተሰርዟል። በመንግሥት ወይም በግል የሥራ ቅጥር ላይ ሰፊ እድልም ይሰጣል" ሲል ለአገሪቱ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፏል።

"መደብ ላይ እናተኩር"

መምህሩ እንደሚለው መንግሥት ለመደብ ልዩነት ትኩረት መስጠት አለበት።

"መንግሥት የዘር ሀረጋችን ላይ ሳይሆን ምን አይነት ሥራና አገልግሎት እንደምንፈልግ ለማወቅ መሞከር አለበት" ይላል።

ማንነትን መሠረት ያደረገ መድልዎ ተወግዶ እኩል እድል እንዲፈጠር ይሻል።

የቀድሞ የጋዜጣ አርታኢ ራይልድ ፊሸር "ለመደብ ቅድሚያ ከሰጠን የበርካታ ጥቁሮችን ሕይወት መለወጥ እንችላለን" ይላል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የያዙት ጥቁሮች ቢሆኑም በድህነት የሚኖሩትም ጥቁሮች እንደሆኑ ያጣቅሳል።

በ1970ዎቹ የጸረ አፓርታይድ ትግል ሲፋፋም ከመብት ተሟጋቹ ስቲቭ ቢኮና የተማሪዎች ሕብረት ጋር አብሮነታቸውን ያሳዩት አፍሪካዊ፣ ሕንዳዊና ክልስ በሚል ተከፋፍለው የነበሩት ባጠቃላይ ነበሩ።

"ጥቁር ነን"

መምህሩ ክስ ሲመሰረትበት የደቡብ አፍሪካ አስተማሪዎች ማኅበር ደግፎታል።

የማኅበሩ ቃል አቀባይ ጆናቮን ረስቲን "አብዛኞቻችን በአፓርታይድ ዘመን የነበረውን የዘር ክፍፍል ላለመቀበል መርጠናል። ራሳችንን የምናየው እንደ ጥቁር፣ አፍሪካዊ፣ ደቡብ አፍሪካዊ ነው " ይላሉ።

አንዳንዶች የዙሉ፣ የኮሳ፣ የአፍሪካን እና ሌሎችም ጎሳዎች አባልነታቸውን በማንነታቸው ውስጥ አጉልተው እንደሚያዩም አያይዘው ያስረዳሉ።

የደቡብ አፍሪካውያን የምጣኔ ሀብት ትስስር ኮሚሽነር ዞእዋ ንቴሊ፤ መንግሥት በቀደመው ሥርዓት ከነበረው የዘር ክፍፍል መላቀቅ አለበት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በዘመነ አፓርታይድ አፍሪካውያን፣ ሕንዳውያን እንዲሁም ክልስ ሰዎች ይደርስባቸው የነበረው መድልዎና ጫና ዛሬም ድረስ ነጮች የምጣኔ ሀብት የበላይነቱን እንዲይዙ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።

"ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ማንም በዘርና በፆታ ምክንያት ማዳላት አይችልም። መብትን መንፈግና መጨቆን ሕገ ወጥ ነው" ይላሉ።

የጥቁሮች የቢዝነስ ካውንስል ኃላፊ ኪጋንኪ ማራቤኒ፤ ደቡብ አፍሪካ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መተዳደር ከጀመረች 27 ዓመታት ቢቆጠሩም፤ አሁንም ያለፈው ዘመን ጫና ሙሉ በሙሉ እንዳልተወገደ ይናገራል።

"የተፈጠረውን ክፍተት ማጥበብ ችለናል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። በጆሀንስበርግ የአክስዮን ገበያ የመጀመሪያውን 100 ደረጃ ከያዙት 75 በመቶ የሚሆኑት ነጭ ወንዶች ናቸው" ይላል።

እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጠው፤ ከመደብ ይልቅ ለቆዳ ቀለም ትኩረት መስጠትን ነው። አፓርታይድ ያደረሰው የዘር መድልዎ ሊሸረሸር የሚችለው ዘርን መሠረት ባደረገ የእኩልነት እርምጃ እንደሆነም ያምናል።

ኬፕ ታውን ውስጥ የሚኖሩና ክልስ የሆኑ ሰዎች 2018 ላይ በፌስቡክ ንቅናቄ ጀምረው ነበር።

መሪው ፋዲል አዳምስ እንዳለው፤ በማንነታቸው የተነሳ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነታቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

በአካባቢው ቁጥራቸው ብዙ ቢሆንም ሥራ ሲቀጠሩ አይስተዋልም።

የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ኤኤንሲ የዘር ልዩነትን እንዳሰፋ የሚተቹ አሉ።

"ኤኤንሲ ክልስ ነን የሚሉ ሰዎችን ያካተተ አካሄድ አልተከተለም " ሲል ይተቻል።

የሥነ ልቦና ምሁር ዶ/ር ሳት ኩፐር፤ ለዘር ልዩነት የተሰጠው ቦታ የሰው ልጅ በሰውነቱ ቅድሚያ እንዳያገኝ መሰናክል እንደሆነ ያምናሉ።

"ከምንም ነገር በፊት ሰው መሆናችንን ዘንግተናል። ለቆዳ ቀለምና ሌሎች መገለጫዎች ነው ቅድሚያ የምንሰጠው። በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በሌላም መስፈርት ልዩነታችንን እናሰፋለን" ሲሉ ያስረዳሉ።

ደቡብ አፍሪካዊ ማንነት ለሚለው ዋጋ መሰጠት እንዳለበትና ልዩነትን የሚያሰፉ ክፍፍሎችን መንግሥት ማስወገድ እንደሚገባው ያሳስባሉ።