የዓለም መሪዎች ባይደንን ምን አሏቸው?

የዓለም መሪዎች አዲሱን የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደንን እንኳን ደስ አለዎት እያሉ ነው።

ለአራት ዓመታት ከዘለቀው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በኋላ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማደስም ተስፋ አድርገዋል።

በርካታ መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥ፣ ኮሮናቫይረስና ሌሎችም ጉዳዮችን በተመለከተ ከባይደን ጋር ተባብረው ለመሥራት እንደሚሹ ተናግረዋል።

የተለያዩ አገራት መሪዎች ለባይደን ያስተላለፉትን መልዕክት እንመልከት፦

ቦሪስ ጆንሰን

የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን "ከባይደን ጋር አብሬ ለመሥራት ጓጉቻለሁ። በአገሮቻችን መካከል ያለውን ግንኙነት እናጠናክራለን። በደህንነት፣ ወረርሽኙን በመዋጋትና በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በጋራ እንሠራለን" ብለዋል።

ጀስቲን ትሩዶ

የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ፤ ወረርሽኙን ለመግታት ሁለቱ አገራት ተባብረው መሥራት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

"ምጣኔ ሀብታችን እንዲያገግም እና ዜጎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ እናደርጋለን። አካታችነትን እናበረታታለን። መካከለኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር፣ በመላው ዓለም ዴሞክራሲና ሰላም ለማስፈንም እንሠራለን" ሲሉም ለባይደን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የአውሮፓ ኮሚሽን

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዘዳንት ቮን ደር ሌይን "አሜሪካ ተመልሳለች። አውሮፓም በተጠንቀቅ እየጠበቀች ነው። ከታማኟ የቀድሞ ወዳጃችን ጋር እንደ አዲስ ተባብረን ከባይደን ጋር በጋራ እንሠራለን" ብለዋል።

የቻይናው አምባሳደር

በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር ቹ ቲካኒ፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳለጥ ከባይደን ጋር ተባብረው እንደሚሠሩ ገልጸዋል። ይህም የኅብረተሰብ ጤና እና የአየር ንብረት ለውጥን ይመለከታል።

የጀርመን ፕሬዘዳንት

የጀርመኑ ፕሬዘዳንት ፍራንክ ዋልተር ስቴንሚር "ዛሬ ለዴሞክራሲ ቀን ወጣ" ብለዋል። አሜሪካ በርካታ መሰናክሎች ገጥመዋት እንደነበርና አገሪቱን ለመፈረካከስ የተደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ አስምረውበታል።

"ጆ ባይደን ቃለ መሐላ ፈጽመው ዋይት ሀውስ በመግባታቸው እፎይታ ተሰምቶኛል። ጀርመናውያንም የኔን ስሜት ይጋራሉ" ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።

ኢማኑኤል ማክሮን

የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ዛሬ በአሜሪካውያን ታሪክ ትልቅ ቀን ነው። አብረናችሁ ነን። በጋራ መሰናክሎችን እናልፋለን። እንኳን ወደ ፓሪሱ ስምምነት ተመለሳችሁ" በማለት ነው የተናገሩት።

የሩስያ አምባሳደር

በአሜሪካ የሩስያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶቭ፤ የባይደንን በዓለ ሲመት እንደተከታተሉ ተናግረው "በአሜሪካ ታሪክ አዲስ ገጽ ነው። የሩስያና የአሜሪካ ግንኙነትም ታድሷል" ሲሉ ሐሳባቸውን አስረድተዋል።

ጁሴፔ ኮንቴ

የጣልያኑ ጠቅላይ ሚንስትር ጁሴፔ ኮንቴ ከባይደን ጋር አገራቸው ተባብራ እንደምትሠራ ተናግረዋል። እንደ ጂ-20 ፕሬዘዳንትነታቸው ከአሜሪካ ጋር የጋራ አጀንዳ እንዳላቸው አስታውሰው፤ ማኅበራዊ አካታችነት እና አረንጓዴ ልማትን በተመለከተ የጋራ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ደቡብ ኮርያ

የደቡብ ኮርያው ጠቅላይ ሚንስትር ሙን ጄኢን "ጆ ባይደን እንኳን ደስ አለዎት። አሜሪካ ተመልሳለች። ዴሞክራሲን ከዚህም በላይ እናበለጽገዋለን" ብለዋል።

ጃፓን

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ዮሺዴ ሱጋ ጆ ባይደንን እንዲሁም ምክትላቸው ከማላ ሐሪስን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋቸዋል። የሁለትዮሽ ትብብሩን ለማሳደግ እንደሚጣጣሩም አያይዘው ጠቅሰዋል።

ታይዋን

የታይዋኑ ፕሬዘዳንት ሲ ኢንግዋን በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትስስር እንደሚጠናከር ቃል ገብተው፤ የባይደን ፓሊሲዎች ሲተገበሩ ለማየት እንደሚሹ ጠቁመዋል።

ንሬንደራ ሞዲ

የሕንዱ ፕሬዘዳንት ንሬንድራ ሞዲ፤ በሕንድና አሜሪካ መካከል የጋራ አጀንዳዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ "የምጣኔ ሀብትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስራችንን እናጠናክራለን" ብለዋል።

አየርላንድ

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ሚካኤል ማርቲን "ባይደን የአየርላንድ የዘር ግንድ አላቸው። ታሪክ ከሳቸው ብዙ ይጠብቃል። ስኬታቸው እኛንም ያኮራናል" ሲሉ ነበር መልዕክት ያስተላለፉት።

ስኮት ሞሪሰን

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን "ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተም አንስቶ መልካም ወዳጆች ነን። በቀጠናው ሰላም፣ በአየር ንብረት ለውጥና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ተባብረን እንሠራለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጀሲንዳ አርደን

የኒው ዚላንዷ ጠቅላይ ሚንስትር ጀሲንዳ አርደን ሁለቱ አገሮች የጋራ ኢንቨስትመንቶች እንዳሏቸው ተናግረዋል። ባይደን አሜሪካን ወደ ዓለም ጤና ድርጅት አባልነት መመለሳቸውንም አሞግሰዋል።

ቤንያሚን ኔታንያሁ

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ባይደን እና ሐሪስ እንኳን ለታሪካዊ ቀን አደረሳችሁ። እኔና ባይደን ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት አለን። የጋራ ችግሮቻችንን ፈትተን የእስራኤልና አሜሪካን ግንኙነት እናጠናክራለን" ብለዋል።

ሐሰን ሮሀኒ

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሮሀኒ "የአምባገነኑ ዘመን አክትሟል። ባይደን ወደ ሕጋዊ አሠራር ተመልሰው ያለፉትን አራት ዓመታት ጠባሳ ያስወግዳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ፓፕ ፍራንሴስ

ፓፕ ፍራንሲስ የባይደን አስተዳደር ፓለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና የሥነ ምግባር ዋጋ የጎላበት እንደሚሆን ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። "የጥበብ መጀመሪያ የሆነው እግዚአብሔር በአገሩ ሰላም እንዲያሰፍንና ለመላው ዓለም በጎ ነገር እንዲያመጣ እጸልያለሁ" ሲሉም ተመኝተዋል።

ዳላይ ላማ

የቲቤት የሃይማኖት አባት ዳላይ ላማ፤ ዓለም የገጠማትን የአየር ንብረት ለውጥ ችግር አንስተው፤ ባይደን ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታቸው አመስግነዋቸዋል።