በማዕድን ጉድጓድ ውስጥ የታፈኑ ቻይናውያን የላኩት ማስታወሻ ተስፋ ፈንጥቋል

ከሳምንት በፊት በቻይና የወርቅ ማዕድን ማውጫ ከደረሰ ፍንዳታ በኋላ ከምድር በታች ታፍነው የሚገኙት 12 ማዕድን አውጪዎች በሕይወት መኖራቸውን አስታወቁ።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፤ ሠራተኞቹ አደጋው ከደረሰ ከሰባት ቀናት በኋላ ለሕይወት አድን ሠራተኞች "እኛን ለማግኘት ሙከራችሁን አታቁሙ" የሚል ማስታወሻ መላክ ችለዋል።

የሌሎች 10 ማዕድን አውጪዎች ዕጣ ፈንታ ግን እስካሁን አልታወቀም፡፡

በቻይና የማዕድን አደጋዎች የተለመዱ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ በደንብ ባልተተገበሩ የደህንነት ደንቦች ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው፡፡

22ቱም ሠራተኞች በምስራቅ ቻይና ሻንዶንግ አውራጃ በያንታይ አቅራቢያ በሚገኘው ሁሻን የማዕድን ማውጫ ጣቢያ ላይ በደረሰው ፍንዳታ ነው የታፈኑት። ፍንዳታው የማዕድን ማውጫውን መውጫ እና የግንኙነት ሥርዓት የጎዳ ሲሆን ጉዳቱን ለማስተካከል እየተሠራ ነው፡፡

የመንግሥት ሚዲያዎች እንደዘገቡት የነፍስ አድን ሠራተኞች ከአንዳንድ ማዕድን አውጪዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ ችለዋል፡፡

ወደ ጉድጓዱ ያወረዱት ገመድ ሲጎትት ከተሰማቸው በኋላ ምግብ፣ መድሃኒት፣ ወረቀት እና እርሳሶች ልከዋል፡፡

ከጉድጓዱ በተሰጣቸው ማስታወሻ በጻፉት መሠረት፤ 12 ሰዎች በማዕድን ማውጫው መካከለኛ ክፍል ውስጥ በሕይወት እንዳሉ የገለጹ ሲሆን የተቀሩት አስር ሰዎች ሁኔታ ግን ግልጽ አይደለም፡፡

12ቱ ማዕድን አውጪዎች የህመም ማስታገሻ እና ተጨማሪ መድሃኒቶች መጠየቃቸውም ተገልጻል፡፡

በተጨማሪም ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

እንደ ቻይና ሚዲያ ዘገባ ከሆነ ከመግቢያው ወደ 600 ሜትር ርቀው ይገኛሉ የተባሉት ሠራተኞችን ለማዳን ተጨማሪ ማውጫ መስመሮች እየተቆፈሩ ነው፡፡

መጀመሪያ ላይ አደጋው ሪፖርት እስኪደረግ ከአንድ ቀን በላይ በመፍጀቱ የነፍስ አድን ሠራተኞች የማዕድን ሠራተኞቹን ለመድረስ እንዲዘገዩ ተገደዋል ተብሏል፡፡

የአከባቢው የኮሚኒስት ፓርቲ ፀሐፊ እና ከንቲባ በዚህ የ30 ሰዓት የመረጃ ልውውጥ መዘግየት ምክንያት ከሥራ ታግደዋል፡፡

በቻይና የማዕድን አደጋዎች ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት የደህንነት ደንቦች በአግባቡ ካለመተግበር ጋር የተቆራኙ ናቸው፡፡

ባለፈው ዓመት ታህሳስ በድንጋይ ከሰል ማዕድን ማውጫ የካርቦን ሞኖክሳይድ አፈትልኮ 23 የማዕድን ሠራተኞች ሞተዋል፡፡

በመስከረም ወር በቾንግኪንግ ዳርቻ በሚገኝ ሌላ የማዕድን ማውጫ ስፍራ 16 ሠራተኞች ሕይወታቸው አልፏል፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ ታህሳስ 2019 በደቡብ ምዕራብ ቻይና በጊዡ ግዛት በከሰል ማዕድን ማውጫ ስፍራ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 14 ሰዎች ሞተዋል፡፡