ሱዳን ዳርፉር ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት 83 ሰዎች ተገደሉ

በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር ግዛት በሁለት ጎሳዎች መካከል በተነሳ ግጭት በትንሹ 83 ሰዎች ተገድለዋል።

የሱዳን ዜና አገልግሎት የሐኪሞች ማኅበርን ጠቅሶ እንደጻፈው ግጭቱ በዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኢል ገነይና ቅዳሜ ዕለት ነው የተከሰተው።

የግጭቱ መነሻ አንድ ሰው በጩቤ ተወግቶ መገደሉ ነው ተብሏል።

አሁን ግጭቱን ተከትሎ በዳርፉር ሰዓት እላፊ የታወጀ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱላሒ ሐምዶክ አንድ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ግጭቱን እንዲመረምር ወደዚያው ልከዋል።

በፈረንጆች በ2003 ዓ/ም የጀመረው የዳርፉር ግጭት በሚሊዯን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰላም አስከባሪ ኃይል ገብቶ የማረጋጋት ሥራ ሰርቷል። የሰላም ንግግሮችም ቀጥለዋል። ሆኖም አሁንም ውጥረቱ እንዳለ ነው።

የቅዳሜ ግጭት የተቀሰቀሰው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኀብረት የሰላም ማስከበሩን ተግባር ለ13 ዓመታት ካስጠበቁ በኋላ ለሱዳን አስረክበው መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ በኢል ገነይና ከተማ የአረብ ዝርያ ያላቸው አርብቶ አደሮች አረብ ካልሆኑት ቡድኖች ጋር ተጋጭተው ደም ፈሷል።

የቅዳሜው ግጭት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ብቻ ሳይሆን መቶ ስድሳ ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስባቸው ያደረገ ነው።

ግጭቱ በካምፕ ውስጥ ተጀምሮ በኋላ ላይ ግን የታጠቁ ሚሊሻዎችን እንዳሳተፈ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ብዙዎቹን በዳርፉር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ያሳተፈ የሰላም ስምምነት የተፈረመው ባለፈው ዓመት ነበር። ሆኖም ስምምነቱ ሁሉንም ተፎካካሪ ኃይሎችና ጎሳዎችን ያሳተፈ አልነበረም።

በዓለም ላይ ከፍተኛ መፈናቀልን አስከትሏል ከሚባሉ ግጭቶች አንዱ የዳርፉር ጦርነት ነው። የአረብ ዘርያ ባላቸውና አረብ ባልሆኑ ጎሳዎች መካከል በሚቀሰቀስ የጥቅም ግጭት በርካቶች ጭዳ ሆነዋል።

የአረብ ዝርያ ያለባቸው ወታደሮችን የሚዘወረው አደገኛው የጃንጃዊድ ሚሊሻ ገድሏቸዋል የሚባሉ መቶ ሺህዎች አሁንም ድረስ ፍትሕ አላገኙም።

ኦማር ሐሰን አልበሽር ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት በተቀሰቀሰው ግጭት 300ሺህ ሰዎች በግጭቱ ተገድለው 2 ሚሊዯን ተኩል ሕዝቦች ተፈናቅለዋል።

አልበሽር በጦር ወንጀል ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የክስ ወረቀት እንዲቆርጥባቸው ያደረገውም ይኸው ነበር።

አልበሽር በ2019 በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣናቸው ሲነሱም በተቃውሞ እንቅስቃሴው የዳርፉር ጉዳይ ትልቅ የቅስቀሳ አጀንዳ ሆኖ ነበር።

በቅርቡ ለቅቆ የወጣው የዳርፉር የሰላም አስከባሪ ቡድን ኢትዮጵያ ተሳትፋበት እንደነበር አይዘነጋም።