ትግራይ ፡ የመብራትና የስልክ አገልግሎት መቼ ይጀምራል?

በትግራይ ክልል መብራት፣ ስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት እስካሁን መልሶ ሥራ ባልጀመረባቸው አካባቢዎች ውስጥ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹ አገልግሎቶቹን እንደሚያገኙ የመብራት ኃይልና የኢትዮቴሌኮም ኃላፊዎች ለቢቢሲ ገለፁ።

ከሁለት ወራት በፊት በክልሉ በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩት የመብራት፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በከፊል የተመለሱባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም፤ በበርካታ ከተሞች ውስጥ እስካሁን አለመመለሳቸውን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

አገልግሎቶቹን መልሶ በቶሎ ለማስጀመር ያልተቻለው በመሠረተ ልማቶቹ ላይ "የደረሰው ውድመት በጣም ከፍተኛ" የሚባል በመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያዎች መስመሮች በመቆረጣቸውና ኢንሱሌተሮች [የኃይል ተሸካሚዎቹ እንዳይነካኩ የሚያደርጉ ስኒዎች] በመሰባበራቸው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌትሪክ ኃይል ተቋርጦ ቆይቷል።

የስልክና ኢንተርኔት አቅርቦትን በተመለከተም የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩም በክልሉ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሱ ከፍተኛ ጉዳቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አስካሁንም ጥገና እየተካሄደ መሆኑንና "ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንደልብ ተንቀሳቅሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥገናዎችን ማድረግ ያስቸጋሪ ስለነበር" በቶሎ ሥራ ማስጀመር አለመቻሉን ተናግረዋል።

እየተጠናቀቀ ባለው ሳምንት በበርካታ አካካቢዎች ከፍተኛ የጥገና ሥራዎች ተከናውነዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ አገልግሎት ለመጀመር መደበኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መብራት የሚያስፈልግ ቢሆንም በአማራጭነት ግን ጄኔሬተርና የፀሐይ ኃይልን እየተጠቀሙ መሆኑን አስረድተዋል።

ጥገና በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች አገልግሎት ለመስጠት ተቃርበናል ያሉት ኃላፊዋ፣ መቀለ የስልክና የብሮድ ባንድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አመልክተው በዚህም ምክንያት የባንክ አገልግሎት በከተማዋ ማስጀመር መቻሉን ገልፀዋል።

በተጨማሪም በማይጨው፣ ዳንሻና በሁመራ የስልክ አገለግሎት መጀመሩን አስታውሰዋል።

ከአላማጣ ጀምሮ በሁመራ በኩል እስከ ሽሬ አካባቢዎች በነበሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን የሚናገሩት አቶ ሞገስ በበኩላቸው፣ በዚህ ምክንያት የተቋረጠውን የኃይል አቅርቦት ለመመለስ ከፍተኛ የሆነ መስመር የመጠገን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የሚያስተዳድራቸው የስርጭት መስመሮች፣ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት "አገልግሎት በፍጥነት መስጠት እንዳይችሉ" በሚያደርግ ሁኔታ ጉዳትና ዘረፋ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

ከፍተኛ የኃይል መስመሮችን እንዲሁም የስርጭት መስመሮቹን ጠግኖ ሥራ ለማስጀመር የጥገና ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ያስረዱት ዳይሬክተሩ፤ በአላማጣ፣ በማይጨው፣ በመሆኒ፣ በአሸጎዳ እና በመቀለ እና በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ ትንንሽ ከተሞች የኤሌትሪክ አገልግሎት አግኝተዋል ብለዋል።

ነገር ግን እስካሁን አክሱም፣ አድዋ፣ ሽሬ፣ ሽራሮ እና ወልቃይት አካባቢዎች ባሉ መሠረተ ልማቶች ላይ "የደረሰው የጉዳት መጠን ከፍተኛ በመሆኑ" የኤሌትሪክ ኃይል አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ጥገናው ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች መካከል አክሱም፣ ሽሬ፣ አድዋ፣ አካባቢዎች የተወሰኑ ሥራዎች እንደሚቀር እና እርሱን ለማተናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም "የተለየ ነገር የማይኖር ከሆነ በአጭር ቀናት ውስጥ፣ . . . በሳምንታት እድሜ ውስጥ" የአክሱምና የአድዋ አካባቢዎች ኃይል የሚያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ ገልፀው፣ ቀኑን ግን ከማስቀመጥ ተቆጥበዋል።

የኢትዮቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ በበኩላቸው የትግራይን ክልል የሚያገለግሉት ዋነኛው ማዕከላት (ኮር ሳይት) የሚገኙት መቀለና ሽሬ ውስጥ እንደሆነ አመልክተው፤ ከመቀሌ አቢይ አዲ ያለው ኦፕቲካል መስመር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንን ለመጠገን ረዥም ጊዜ መውሰዱን የተናገሩት ኃላፊዋ በአሁኑ ጊዜ 98 ኪሎ ሜትር ያህል የመስመር ጥገናው ተከናውኖ መጠናቀቁን ገልፀው፤ ሽሬ ላይ ያለውን ማዕከል (ኮር ሳይት) ሥራ ለማስጀመር ከአብይ አዲ ወደ ሽሬ ያለውን መስመር መጠገን እንደሚጠበቅ ጨምረው ተናግረዋል።

ወደ አደዋ ባለው መስመር ላይ ደግሞ ጥገናው ቢካሄድም ውቅሮ በአንዳንድ አካባቢዎች ባሉ የቴሌኮም ማማዎች [ታወሮች] ላይ የሚገኙ እቃዎች በመዘረፋቸው እነዚህ እቃዎች የማሟላት ሥራን ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ውቅሮ፣ አዲግራት፣ ነጃሺ አካባቢ በጣም አነስተኛ ሥራዎች ብቻ መቅረታቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ገልፀው በቅርቡ አገልግሎት ይጀምራሉ ብለዋል።

አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው መሥሪያ ቤታቸው በክልሉ ያለው የኃይል አቅርቦትን ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ የሚካሄደው ጥገና በኃይል ተሸካሚዎችና በስርጭት መስመሮች ላይ በመሆኑ ሥራው ጎን ለጎን እየተገናኘ እንዲሄድ ማድረግ ካልተቻለ የአንዱ ሥራ መጠናቀቅ ብቻውን ለከተሞቹ የኃይል አቅርቦት ማግኘት ወሳኝ አለመሆኑን አስረድተዋል።

በደንነት ስጋት ውስጥ ሆነው የሚሰሩ ባለሙያዎች

የመስመር ጥገናው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች አሁንም ጥቃት ፈጽመው የሚሸሹ ቡድኖች መኖራቸውን የገለፁት ኃላፊዎቹ፣ እስካሁን በድርጅቱ ሠራተኞች ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም እንደዚህ አይነት ክስተቶች ሥራቸውን እንደሚያስተጓጉሉ ጨምረው ገልፀዋል።

በተጨማሪም የእንቅስቃሴ ገደብ መኖሩ፣ በመሠረተ ልምቶቹ ላይ የደረሱት ውድመቶች ከፍተኛ የሚባሉ መሆናቸው ተደማምረው አሁን የሚያከነውኑትን ጥገና ከባድ እንዳደረገውና ለነዋሪው በፍጥነት የኤሌትሪክ እና የስልክ አገልግሎቶችን ማቅረብ እንዳይችሉ ማድረጉን ተናግረዋል።

ሥራው "ኃላፊነት እና አደጋ ያለበት" ያሉት አቶ ሞገስ፣ በተረጋጉት አካባቢዎች ሥራዎች ቢጠናቀቁም አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ መስተጓጎሎች ደግሞ ሥራው መቼ ተጠናቅቆ አገልግሎት ማቅረብ እንደሚቻል ቁርጥ ያለ ቀን ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ማድረጉን ተናግረዋል።

አሁንም የጥገና ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለፁት አቶ ሞገስ ከመቀለ ተነስቶ ወደ አክሱምና አደዋ በየዕለቱ በመሄድ ባለሙያዎቻቸው በአስቸጋሪ የመልከ አምድር አቀማመጥ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

የቴሌኮም አገልግሎትን መልሶ ለማስጀመር የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወትም ሲናገሩ በአካባቢው የቴሌኮም መስመሮች ላይ "ከፍተኛ ጉዳት ነው የደረሰው፣ በርካታ እቃዎች ጎድለዋል ተዘዋውሮ ለመስራት የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ አመቺ አይደለም" በማለት እስካሁን ግን ከፍተኛ ሥራዎችን መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ባለሙያዎቻቸው በክልሉ ያለውን አገልግሎት ለማስጀመር ቀን ተሌት እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ፣ ጥገና የተደረገባቸውና አስፈላጊ ነገሮች የተሟሉላቸው አካባቢዎች ሥራው እንደተጠናቀቀ የተወሰኑ ቦታዎች አገልግሎት ይጀምራሉ ብለዋል።

ጨምረውም እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ የተወሰኑ ስፍራዎችን ፈጥኖ ለማስጀመር እየሰሩ መሆኑን ገልፀው፣ በርካታ ስፍራዎች በወር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ሪጅን ቅርንጫፍ 746 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን እስካሁን ድረስ 699 ሠራተኞቹ ወደ ሥራ ገበታቸው መመለሳቸውን ኃላፊዋ አስታውሰዋል።

የደረሰው የጉዳት መጠን ይታወቃል?

አቶ ሞገስ ስለደረሱት ጉዳቶች ለቢቢሲ ሲያስረዱ ከአላማጣ ወደ ማይጨው፣ መሆኒ፣ መቀለ እንዲሁም ከአሸጎዳ ወደ አክሱም እና ሌሎች የክልሉ ከተሞች የሚሄዱት አብዛኞቹ የ230 ኪሎ ቮልት ኃይል ተሸካሚ መስመሮች መሆናቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ መስመሮች በዋናነት 230 ኪሎ ቮልት ተሸካሚ ቢሆኑም ክልሉ ላይ የተለያዩ አካባቢዎችን የሚያዳርሱ 11 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ገቢና ወጪ መስመሮች አሉ።

ከኃይል ማከፋፈያዎቹ ውጪ የድርጅቱ ሠራተኞች ተዘዋውረው በተመለከቷቸው መስመሮች ላይ "ከፍተኛ ጉዳት" መድረሱን አቶ ሞገስ ገልፀዋል።

መስመሮቹ በተለያየ ስፍራ የተለያየ የጉዳት መጠን ስለደረሰባቸው፣ የደረሰውን የጉዳት መጠንን አስልቶ ለመናገር እንደሚያስቸግር ገልፀው "የጉዳቱ መጠን ግን ከፍተኛ ነው" ሲሉ ገልፀውታል።

ሁሉም ውድመት የደረሰባቸው አካባቢዎች ለጥገና አለመድረሳቸውን በመግለጽም በገንዘብ የደረሰው ኪሳራ መጠንን እንዲሁም ለጥገና ያስወጣውን አጠቃላይ ወጪ አሁን ለመናገር እንደሚያስቸግራቸው ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ጥቅምት መጨረሻ ላይ የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የኤልክትሪክ ኃይልና የቴሌኮም አገልግሎቶች ተቋርጠው ቆይተዋል።

ምንም እንኳን የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የክልሉን ዋና ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ በመቀሌና በአንዳንድ አካባቢዎች ግን አሁን ድረስ አገልግሎቶቹ እንደተቋረጡ መሆናቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የኤልክትሪክና የስልክ አገልግሎቶችን በመላው አገሪቱ የሚያቀርቡት ሁለቱ ተቋማትም በክልሉ ውስጥ አገልግሎታቸውን መልሰው ለማስጀመር እጣሩ መሆናቸውን እየገለጹ ነው።