ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በ2020 በስፖርት ሜዳዎች ላይ የተስተዋሉ የተቃውሞ ምልክቶች
በፈረንጆቹ 2000 የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ "ስፖርት ዓለምን የመቀየር ኃይል አለው" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ በ2020 ይህ እውን ሆኖ ታይቷል።
ያለፈው የፈረንጆቹ ዓመት [2020] በሁሉም የስፖርት ዘርፎች ያሉ የዓለማችን ስፖርተኛ ዓለምን ለመቀየር ቆርጠው የተነሱበት ነበር።
ዘረኝነት ይብቃ ሲሉ ጮኸዋል። ለውጥ ይምጣ ሲሉም ጠይቀዋል።
ሴራሊዮናዊው አጥቂ ኬይ ካማራ በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር ነው የሚጫወተው። የቀድሞ ክለቡ ከኮሎራዶ ራፒድስ ሚኒሶታ ዩናይትድን ተቀላቅሏል።
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ እጅ በግፍ መገደሉን ተከትሎ ተቃውሟቸውን ካሰሙ ተጫዋቾች መካከል ነው ካማራ።
"የልጆቼ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ነው አቋሜን በይፋ እንድገልፅ ያደረገኝ" ይላል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።
ከአሜሪካ አልፎ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወቱ እግር ኳሰኞች ዘረኝነትን በመቃወም መንበርከክ የጀመሩት በ2020 ነው።
አሜሪካዊቷ የዝላይ ውድድር ክብረ-ወሰን ባለቤት ቶሪ ፍራንክሊን እንደምትለው ስፖርት በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል።
አልፎም ዘረኝነት ለመዋጋት በሚደረገው ፍልሚያ የስፖርት ሚና የሚናቅ አይደለም ትላለች።
"እኔ ስፖርት ትልቅ ተፅዕኖ ማምጣት እንደሚችል ነው የማስበው" ትላለች ፍራንክሊን።
"በአሜሪካ ባህል ስፖርት ትልቅ ቦታ አለው። በቴሌቪዥን ሰፊ ሽፋን ይሰጠዋል። መገናኛ ብዙሃን ይዘግቡታል። ለዚህ ነው ዘረኝነትን በመቃወም እጃችንን ስናነሳ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን የምለው።"
ባለፈው ነሐሴ የአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ክለብ ሚልዋውኪ ባክስ ተጫዋቾች ከኦርላንዶ ማጂክ ጋር የነበራቸውን ጨዋታ ጃኮብ ብሌክ የተሰኘው ጥቁር አሜሪካዊ በፖሊስ ጥይት መመታቱን ተከትሎ አንጫወትም ብለው ነበር።
ብሌክ በፖሊስ ጥይት በተደጋጋሚ የተመታው በቅርጫት ኳስ ክለቡ ስታድየም አቅራቢያ ነበር።
ይህንን ተከትሎ ኤንቢኤ የተባለው የቅርጫት ኳስ አስተዳደር ሌሎችም ጨዋታዎች እንዲሰረዙ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
በወቅቱ በአሜሪካ ቅርጫት ኳስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች እንዲሰረዙ ተደርጎ ነበር።
የሚያነሳሳ ለውጥ
በአትሌቲክስ ዓለም ትልቁ ውድድር የኦሊምፒክ ጨዋታ ነው።
ይህ ውድድር በ2020 ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ይህ ሳይሆን ቀርቷል።
ከዚህ ቀደም በነበሩ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርካታ አትሌቶች ለውጥ ለማምጣት እጃቸውን ወደላይ አንስተው ነበር።
አትሌቶቹ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ለውጦችን የሚጠይቁ ርዕሶችን አንስተዋል።
ነገር ግን ባፈለው ዓመት ጥር የኦሊምፒክ ኮሚቴ አዲስ ሕግጋትን አውጥቷል። ሕጉ አትሌቶቹ በኦሊምፒክ መድረክ ላይ ፖለቲካዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ አሊያም ከዘር ጋር የተገናኘ መልዕክት ማስተላለፍ አይችሉም ይላል።
ኮሚቴው በተለይ ደግሞ በእጅ ምልክት ማሳየትና መንበርከክ ክልክል ነው ብሏል።
የኦሊምፒክ ሕጎችን አልቀበልም ማለት እንደማይቻልም ኮሚቴው አዲስ ባወጣው መመሪያ ላይ አስቀምጧል።
በ2019 በተካሄደው የፓን አሜሪካን ጨዋታዎች ላይ ተቃውሟቸውን እጃቸውን ከፍ በማድረግ ያሳዩ ሁለት አትሌቶች የ12 ወራት ቅጣት ተላልፎባቸው ነበር።
በኦሊምፒክ ሜዳ ከታዩ ታሪካዊ ተቃውሞዎች መካከል አንዱ አሜሪካዊያኒ ቶኒ ስሚዝና ጆን ካርሎስ በ1968 የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ያለ ጫማ፣ በጥቁር ካልሲና ጥቁር ጓንት ሆነው እጃቸውን በማንሳት ተቃውሟቸውን የገለፁበት መንገድ ነው።
አትሌቶቹ በዚህ ድርጊታቸው ዕግድ ተጥሎባቸው ነበር።
ሌላኛው ክስተት የታየው በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ነው። በወቅቱ በማራቶን ውድድር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረው ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሌሊሳ ሁለት እጆቹን ወዳላይ በማንሳት በማጣመር የኦሮሞ ተቃውሞን ያጎላበት መንገድ ነው።
ፈይሳ ይህን ምልክት የተቃውሞ ምልክት ያሳየው በውድድሩ መጠናቀቂያ መስመር ላይና በጋዜጣዊ መግለጫ ቦታ ላይ ነበር።
ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን ወርደው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተተኩ።
ምንም እንኳ ፈይሳ ብቻውን ለውጥ አምጥቷል ባይቻልም በወቅቱ በአገር ቤት የነበረውን ተቃውሞ ለዓለም ሕዝብ በማንፀባረቅ ሚና እንደተጫወተ የሚካድ አይደለም።
ነገር ግን የኮሚቴው መመሪያ መሰል ተቃውሞዎች በምንም ዓይነት መንገድ በኦሊምፒክ መድረክ ላይ እንዲታይ አይፈቅድም።
አሁን ሁሉም ስፖርተኞች ጥያቄያቸው አንድ ነው - ቀጣይ ምን ማድረግ እንችላለን? የሚል።
አብዛኛዎቹ ገና ብዙ መንገድ ይቀረናል ይላሉ። ለውጥ ለማምጣት ስፖርት የበኩሉን መወጣት ይቻል እንጂ ብቸኛው መንገድ እንዳልሆነ በርካቶች ይስማማሉ።
ነገር ግን ታሪክ ስፖርት ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑን መዝግቦ አሳይቶናል።