'በተገባደደው 2020 በዓለም ዙሪያ 53 ጋዜጠኞች ተገድለዋል'

በተገባደደው የፈረንጆቹ 2020 በዓለም ዙሪያ 53 ጋዜጠኞች ተገድለዋል ሲል ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር አስታውቋል።

ማኅበሩ 2020 መገባደዱን አስታኮ ባወጣው የቁጥሮች መረጃ ላይ ነው ይህ ያሳወቀው።

በዚህም መሠረት 46 ጋዜጠኞች፣ 4 የሚድያ ተባባሪዎችና 1 የማኀበረሰብ ጋዜጠኛ እንደተገደሉ መረጃው ይጠቁማል።

ሜክሲኮ 8 ጋዜጠኞች የተገደሉባት አገር በመሆን ቀዳሚውን ሥፍራ ስትይዝ አፍጋኒስታን 4 ሶሪያ ውስጥ ደግሞ ሌሎች 4 ጋዜጠኞች ተገድለዋል።

ኢራን ውስጥ ለአማድኒውስ ይሠራ የነበረው ጋዜጠኛ ዛም ሮላህ በዚህ የተገደለ ብቸኛው የማኀበረሰብ ዜጋ ጋዜጠኛ ነው።

ሶማሊያና ናይጄሪያ ውስጥም ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ተገድለዋል ይላል ማሕበሩ ያወጣው ዘገባ።

የጋዜጠኞች እሥር

በዚህ ዓመት ከተመዘገበው የጋዜጠኞች ሞት ባለፈ በርካታ የሚድያ ሙያተኞች ለእሥር መዳረጋቸውን ማሕበሩ ያወጣው መረጃ ያሳያል።

በማሕበሩ ድረ-ገፅ ላይ እንደሰፈረው መረጃ ከሆነ በዓለም ዙሪያ 264 ጋዜጠኞች በዚህ ዓመት ብቻ ታሥረዋል።

ጋዜጠኞችን በማሠር ወደር አልገኘላትም የተባለችው ቻይና ናት።

ቻይና ውስጥ በ2020 ብቻ 76 ጋዜጠኞች ለእሥር ተዳርገዋል።

ቻይና ከዩገር ሙስሊሞች ጉዳይ ጋር በተያያዘ 'ምስል የሚያጠለሽ' ዜና ሰርታችኋል ያለቻቸውን ጋዜጠኞች ነው ለእሥር የዳረገችው።

ለእሥር ከተዳረጉት ጋዜጠኞች መካከል ቻይናዊያን ሆነው ለውጭ አገራት መገናኛ ብዙሃን የሚሠሩ ይገኙበታል።

ከቻይና በመቀጠል አፍሪካዊቷ አገር ግብፅ 28 ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛዋ ለሚድያ ሰዎች አስፈሪ የሆነች ሃገር ሆናለች።

ሳዑዲ አራቢያ ውስጥ 20 ጋዜጠኞች፣ ኢራን ውስጥ ደግሞ 16 ጋዜጠኛው በተገባደደው ዓመት ለእሥር ከተዳረጉ መካከል ናቸው።

በተጨማሪ ቱርክ 13፤ ሶሪያ ደግሞ 12 ጋዜጠኞች በማሰር በመዝገቡ ላይ ስማቸው ሰፍሯል።

ኢትዮጵያ

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ድረስ ባለው ጊዜ 4 ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ለእሥር መዳረጋቸውን ዓለም አቀፍ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማሕበር ይፋ አድርጓል።

የኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ ጋዜጠኛ ኡዲ ሙሳ፣ የዓል-ዓለም ጋዜጣ ሪፖርተር አብርሃ ሃጎስ፣ የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጠኞቹ ሃፍቱ ገብረእግዚአብሔርና ፀጋዬ ሃዱሽ በአሁኑ ወቅት በእሥር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ሆነው ተመዝግበዋል።

ከጥቂት ቀናት በፊት የታሠረው የሮይተርስ ካሜራ ባለሙያው ኩመራ ገመቹን ጨምሮ ሌሎች ለእሥር መዳረጋቸው የተነገረ ጋዜጠኞች ስም ዝርዝር በማሕበሩ ዘገባ ላይ አልተካተተም።

ሌላኛው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን ሲፒጄ [ኮሚውኒቲ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ] ኅዳር 22/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ሰባት ጋዜጠኞች በሰሯቸው ዘገባዎች ምክንያት እስር ቤት መግባታቸውን ገልጾ ነበር።

ከእነዚህ መካከል አምስቱ የታሰሩት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት ኃይሎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው።

ድርጅቱ ኢትዮጵያ አምና [2019] ጋር ሲነፃፀር ለጋዜጠኞች የተሻለ ነፃነት ሰጥታለች ይላል። አምና ከነበረችበት 119ኛ ደረጃም ወደ 99 ከፍ ማለት ችላለች።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የታየው የተስፋ ጭላንጭል እንዳይጨልም መንግሥት የጋዜጠኞችን ነፃነት ሊያስከብር ይገባል ይላል ማሕበሩ።

ኤርትራ

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኤርትራ ውስጥ 11 ጋዜጠኞች አሁንም ድረስ በእሥር ላይ እንደሚገኙ የጋዜጠኞች ማሕበር አስታውቋል።

ከእነዚህ መካከል ዳዊት ይስሃቅን ጨምሮ 4 ጋዜጠኞች ከ19 ዓመታት በፊት በፈረንጆቹ 2001 ለእሥር የተዳረጉ ናቸው።

ሌሎች አራት ጋዜጠኞች ደግሞ በፈረንጆቹ 2011 ለእሥር ከተዳረጉ ወዲህ ተፈትተው አያውቁም።

ኤርትራ ውስጥ የታሠሩ ጋዜጠኞች የአእምሮና አካላዊ ጤና ሁኔታ እንዲሁም የት እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም።

በዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ደረጃ 178ኛ ላይ የምትገኘው ኤርትራ ለገለልተኛ ሚድያዎች ምንም ዓይነት ነፃነት አትለግስም ሲል ማሕበሩ ይወቅሳል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችው የሰላም ስምምነት በፕሬስ ነፃነት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣም ሲልም ያክላል።