ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
2020 በፎቶ ፡ ከኮሮናቫይረስ ጨረቃ ላይ ሰንደቅ አላማ እስከማስቀመጥ
ዓለም በኮሮናቫይረስ የተፈተነበት የፈረንጆቹ 2020 ሊያበቃ ነው። ዓመቱን ወደኋላ መለስ ብለን በፎቶ ስብስብ እንዲህ ቃኝተናል። ከጥር ወር እንጀምር።
ጥር
ቻይና ዉሃን ውስጥ የተቀሰቀሰው ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ የግድ ነው። ከወራት በፊት በመላው ዓለም የጭምብል እጥረት ተከስቶ ነበር።
የካቲት
በከዋክብት ሳይንስ እጅግ አስደናቂ የሆነው ሙሉ ጨረቃ ቱርክ በሚገኘው ሰልሚዬ መስጂድ አቅራቢያ የታየው በዚህ ዓመት ነው።
መጋቢት
አብዛኛው ሰው ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጓደኛ ለማግኘት እንደ ዙም ያሉ የተለያዩ መተግበሪያዎችን ለመጠቀም ተገዷል። ይህ ፎቶ ሆንግ ኮንግ ውስጥ የሚገኝ መምህር ለተማሪዎቹ በበይነ መረብ ትምህርት ሲያስተላልፍ የተነሳ ነው።
ሚያዝያ
ወረርሽኙን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን የመጠበቅ መርህ በዓለም ዙሪያ ተግባራዊ ሆኗል። አሜሪካ ውስጥ የሚኖሩ የካቶሊክ ቄስ ጸበል ለመርጨት ፈጠራ የተሞላበት መንገድን ተጠቅመዋል።
ግንቦት
ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ እጅ መገደሉ በአሜሪካና በሌሎች አገራትም ዘረኝነትን የሚቃወም ንቅናቄ አስነስቷል።
ሰኔ
እንቅስቃሴ ላይ ገደብ ከመጣሉ በፊት ባርሴሎና ውስጥ በሚገኘው ግሬን ቴትሬ ደል ሊሲዮ ከሁለት ሺህ ለሚበልጡ ችግኞች ሙዚቃ ቀርቧል።
ሐምሌ
ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እንዲሁም በሕንድ፣ በፓኪስታን እና በኢራን ውስጥ የተስፋፋው የአንበጣ መንጋ ስጋት የሆነበት ዓመት ነው። በምስሉ ኬንያ ውስጥ አንዲት ሴት ሰብል በአንበጣ መንጋ ተወሮ ስትመለከት ይታያል።
ነሐሴ
በሊባኖስ መዲና በቤይሩት የተከሰተው ፍንዳታ ኒውክሌር ነክ ካልሆኑ ፍንዳታዎች ሁሉ ትልቁ ነው። ከ200 በላይ ሰዎች ሲሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ፎቶው የሚያሳየው ፒያኖ ተጫዋቹ ሬይመንድ ኢሳያም ከደረሰበት ጉዳት ባሻገር ቤቱን አጥቷል።
መስከረም
የብራዚል አማዞን ጫካ እጅግ በሚያስፈራ ሁኔታ የእሳት አደጋ ደርሶበታል። የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ቃጠሎው አሳስቧቸዋል። አንድ ጃጓር መዳፉ ተቃጥሎ ከእሳቱ ተርፏል።
ጥቅምት
ኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደረባቸው መካከል ነጋዴዎች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ። በጣሊያን መዲና ሮም የሚገኘው ሬስቶራንት የንግዱ መቀዛቀዝ ተምሳሌት እንዲሆን አጽም አስቀምጧል።
ኅዳር
በታይላንድ ተቃውሞ ከሚሳተፉ አንዱ ሚትሬ ቺቲንዳ ነው። ጸጉሩን የተቆረጠው ተቃውሞውን እንደሚደግፍ በሚጠቁም የሦስት ጣት ምልክት ነው። ይህ ምልክት 'ሀንገር ጌምስ' ከተባለው ፊልም የተወሰደ ነው።
ታኅሣስ
ቻይና ጨረቃ ላይ ሰንደቅ አላማዋን በመትከል ከዓለም ሁለተኛዋ አገር ሆናለች። በተጨማሪም ቼንጅ-5 የተባለው የሕዋ ጉዞ ከ44 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጨረቃ አለት አምጥቷል።