የሱዳንና እስራኤል ስምምነት ስጋት የሆነባቸው ስደተኞች

የሱዳኗ ዋና ከተማ ካርቱም በተለያዩ ብሄሮች መከፋፈል የሚታይባት ከተማ ናት። የከተማዋ ዙሪያ የዳርፉር ጦርነትን ሸሽተው የመጡ፣ የኑባ ተራሮችና ሌሎች የተገፉ ማህበረሰቦች የሚኖሩበት ሲሆን የከተማው መሀል ላይ ደግሞ አረብኛ ተናጋሪዎች በብዛት የሚኖሩበት ነው ትላለች ጋዜጠኛዋ ዛይነብ መሀመድ ለቢቢሲ በጻፈችው ደብዳቤ ላይ።

ካርቱም ከዚህ በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 1967 የአረብ ሊግ ስብሰባን ካስተናገደች ወዲህ የአረብ ስምምነት ማዕከል ተደርጋ የምትቆጠር ሲሆን በዚህ ስምምነት መሰረት የአረብ አገራት ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማቋረጥ ተስማምተዋል።

በስብሰባውም ላይ ከእስራኤል ጋር ምንም አይነት ሰላማዊ ግንኙነት ላለማድረግ፣ እውቅና ላለመስጠትና ላለመደራደር ተስማምተዋል።

በካርቱም የሚኖሩ በርካቶችን የሚያማርር አንድ ነገር አለ። በየዓመቱ የናይል ወንዝ እየሞላ በርካታ ቤቶችን ያፈርሳል፣ ጠራርጎ ይወስዳል፣ የሰዎች ሕይወትንም እስከመቅጠፍ ይደርሳል።

ታዲያ በዚህ ወንዝ አቅራቢያ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል ጥቂት የማይባሉት ቤታቸውን መልሰው የሚገነቡት በእስራኤል ጥገኝነት ጠይቀው የሚኖሩ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው በሚልኩላቸው ገንዘብ ነው።

በቅርቡ በአሜሪካው ተሰናባች ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አደራዳሪነት በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ደግሞ በጊዜያዊነት ጥገኝነት ለተሰጠቻቸው በርካታ ሱዳናውያን አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ሱዳን ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ደፋ ቀና ስትል የነበረው አሜሪካ አሸባሪነትን ከሚደግፉ አገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትሰርዛት ለማድረግ እንደሆነ በርካቶች ሲገልጹ ቆይተው ነበር።

ቃላቸውን ጠብቀውም ፕሬዝዳንቱ ሱዳንን ከዚህ ዝርዝር ውስጥ አስወጥተዋታል።

እአአ 1948 ላይ እስራኤል አገር መሆኗን ካወጀች ወዲህ ሱዳን ከአገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ወስና ነበር። የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ባህሬንም ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ እስራኤልና ባህሬን ግንኙነታቸውን ሙሉ በሙሉ ለማሻሻል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ይፋ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነበሩ።

ለበርካታ አስርታት በርካታ የአረብ አገራት እስራኤልን የፍልስጥኤም ጉዳይ ከተፈታ በኋላ ግንኙነታቸውን እንደሚቀጥሉ በመግለጽ አግልለው ነበር።

የሱዳንና የእስራኤልን ስምምነት ተከትሎ በሱዳን መንግስት መከራ ይደርስብናል ብለው በእስራኤል ጥገኝነት ጠይቀው ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሱዳናውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ በሱዳን የደህንንት ሰራተኞች እንደተገረፉ ይናገራሉ።

የሱዳንና የእስራኤልን ስምምነት ተከትሎ የእስራኤል የደህንነት ሚኒስትሩ ኤሊ ኮሀን የሱዳን ጥገኛ ጠያቂዎች ወደ አገራቸው መሄድ እንዳለባቸው ተናግረው ነበር። ነገር ግን አብዛኛዎቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች በሱዳን ያለውን ግጭት ሸሽተው ነው እስራኤል የገቡት።

የተባበሩት መንግስታት እንደሚለው ከ6 ሺ በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች በእስራኤል የሚገኙ ሲሆን በእዛኛዎቹ ደግሞ እስካሁን ድረስ ሕጋዊ የስደተኛ ሰነድ እንኳን ማግኘት አልቻሉም።

እንደውም በቅርብ ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች መጠለያ ካምፖች ውስጥ እንዲኖሩ አልያም እንደ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ባሉ ሁለተኛ አገራት እንዲኖሩ ምርጫ እየተሰጣቸው እየተባረሩ ይገኛሉ።

በአውሮፓውያኑ 2014 ወደ ሱዳን እንዲመለስ የተደረገ አንድ ግለሰብ የመመለስ ውሳኔው እንደሚያስቆጨው ይናገራል። ምክንያቱም ተመላሾች በደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ክትትል የሚደረግባቸው ሲሆን ፓስፖርታቸውም ቢሆን ለአምስት ዓመታት በኃላፊዎች ይያዝባቸዋል።

በአሁኑ ሰአት ታናሽ ወንድሙ እስራኤል ውስጥ የሚገኘው ይሄው ግለሰብ ወንድሙ ፋብሪካ ውስጥ ስራ አግኝቶ ቤተሰቡን እየደጎመ እንደሚገኝ ይናገራል።

አዝራ ኤል ኑር የምትኖረው በእስራኤሏ አራድ ውስጥ ሲሆን ከዚህ በኋላ ወደ ሱዳን የመመለስ ምንም አይነት ፍላጎት የላትም። በኑባ ተራሮች የሚደረገውን ጦርነት ሸሽታ ነው በሰባት አመቷ ከቤተሰቧ ጋር ወደ እስራኤል የተሰደደችው።

በመጀመሪያ ወደ ግብጽ ነበር ያመሩት። የመጀመሪያዎቹን ሰባት ዓመታት በግብጽ በስደተኝነት ያሳለፉ ሲሆን ወደ ሌላ አገር የመዘዋወር እድል እንኳን እንዳልነበራቸው ትናገራለች።

''በመጨረሻም አባቴ ወደ እስራኤል መሄድ እንዳለብን ወሰነ። ወደ እስራኤል ለመሄድ ግን በጣም ከባድ ነበር።''

በአሁኑ ሰአት አዝራ የ27 ዓመት ወጣት ናት። ሁለት ልጆች ያሏት ሲሆን ሁለቱም ልጆቿ መናገር የሚችሉት ኢብራኢስጥኛ ብቻ ነው። ነገር ግን ማንኛቸውም እስራኤል ውስጥ ተረጋግቶ ለመቆየት እንኳን የሚያስችላቸው የስደተኛ ሰነድ አልተሰጣቸውም።

አዝራ ወደ ሱዳን እንዲመለሱ የሚገደዱ ከሆነ እሷና ልጆቿ ለበርካታ ዓመታት የሱዳን ጠላት ተደርጋ ትሳል በነበረችው እስራኤል ኑሯቸውን አድርገው በመቆየታቸው መገለልና መድልዎ ሊደርስባቸው እንደሚችል ትሰጋለች።

''ሁለቱም ሴት ልጆቼ ስለ ሱዳን ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። እኔ እንኳን ስለ አገሬ የማውቀው ነገር በጣም ውስን ነው። ሱዳንን ለቅቄ ስወጣ በጣም ትንሽ ልጅ ነበርኩ። ከዚህ የምንባረር ከሆነ እንዴት አድርጌ መኖር እንደምችል ያማውቀው ነገር የለም'' ትላለች።

ሌላኛው ስደተኛ የ32 ዓመቱ ባሺር ባብኪር ወደ ዳርፉር ተመልሰህ ሂድ እንዳይባል ከፍተኛ ስጋት አለበት። ቤተሰቦቹ አሁንም መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን እሱም እዛው እያለ መጠለያቸው ውስጥ ጥቃት ደርሶበት ነበር።

''ከጥቃቱ በኋላ እዛ ምንም የቀረ ነገር አልንበረም። ወፎች እንኳን ሸሽተው ሄደዋል። ካርቱም ዘመድ ያላቸው ወደዛው ሲሄዱ ምንም ዘመድ ያልነበራቸው ግን ካሳብ የሚባል መጠለያ ውስጥ ቀርተዋል።''

እሱ ከዚህ ክስተት በኋላ በግብጽ በኩል አድርጎ ለአዘዋዋሪዎች ገንዘብ ከፍሎ እስራኤል መግባት ቻለ። ነገር ግን አሁንም ድረስ ወደ አገሩ ሱዳን የመመለስ ከፍተኛ ስጋት አለበት። ምክንያቱም ለበርካታ ሱዳናውያን አሁንም ድረስ እስራኤል ጠላት አገር ናት።

ለዚህ ትልቅ ማሳያ ደግሞ የሁለቱ አገራት ስምምነት ይፋ ከተደረገ በኋላ በርካቶች በአደባባይ በመሰብሰብ ተቃውሟቸውንና ቁጣቸውን መግለጻቸው ነው።

በእስራኤል አፍሪካ ግንኙነት ላይ ምርምር የሚያካሄዱት ዮታም ጊድሮን እንደሚሉት እስራኤል ለበርካታ ዓመታት የካርቱም መንግስትን የሚቃወሙና በደቡብ በኩል ያሉ አማጺያንን ስትደግፍ ቆይታለች።

አሁንም ድረስ ግጭት ባልራቀው የዳርፉር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ አማጺያን የተወካይ ቢሯቸውን እየሩሳሌም ውስጥ ከፍተውም ይንቀሳቀሳሉ።

ነገር ግን እስራኤል ውስጥ ለሚገኙት ሱዳናውያን ሁኔታው እጅግ የተወሳሰበ ነው። እዛው እስራኤልም ስጋት ያለባቸው ወደ አገራቸው ቢሄዱም ምን አይነት ሁኔታ እንደሚጠብቃቸው አያውቁም።

እስራኤል ለጊዜው ወደ ሱዳን መሄድ የሚፈልጉ ብቻ ናቸው የሚሄዱት ብላለች። ነገር ግን ስደተኞቹ በእጅ አዙር ከእስራኤል እንዲወጡ እየተገደዱ እንደሆነ ነው የሚያስቡት።

ለምሳሌም በአውሮፓውያኑ 2017 የወጣውን ረቂቅ ሕግ ይጠቅሳሉ። በዚህ ሕግ መሰረት ስደተኞች ወደ አገራቸው እስከሚመለሱባት ቀን ድረስ አሰሪዎች የስደተኞችን 20 በመቶ ደሞዝ እንዳይከፍሏቸው የሚል ሀሳብ ቀርቧል።

ነገር ግን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሚያዝያ ወር ላይ ውድቅ አድርጎታል።

''ወደ ዳርፉር እንድንመለስ የሚደረግ ከሆነ ልንሞት እንችላለን፤ እስራኤል አሁንም ለበርካታ ሱዳናውያን ጠላት አገር ነው። ነገር ግን እዚህም ያለው ሁኔታ በጣም አሰቃቂ ነው'' ይላል ባሺር ባብኪር።