ኮሮናቫይረስ ፡ ኬንያ 24 ሚሊየን 'ዶዝ' ክትባት ማዘዟ ተነገረ

ኬንያ 24 ሚሊየን የኮቪድ-19 ክትባት ብልቃጦችን ማዘዟን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘ ስታር ጋዜጣ ዘገበ።

የኬንያ መንግሥት 10 ቢሊየን የኬንያ ሽልንግ (89 ሚሊየን ዶላር) ገንዘብ ለክትባቱ እንደሚያወጣም ጋዜጣው አስነብቧል።

ይሁን እንጅ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር የትኛውን ክትባት እንዳዘዘች የተገለፀ ነገር የለም።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የጤና ሚኒስቴር ክትባቱን ለማግኘት በዓለም ዙሪያ ክትባትና የጤና አገልግሎት ማስፋፊያ ፕሮግራሞችን ለሚረዳው የዓለም አቀፍ ለጋሾች ጥምረት በእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃሉ 'ጋቪ' ጥያቄ ያቀረበው ባሳለፍነው ሳምንት ነበር።

ኬንያ ያዘዘችው የክትባት መጠንም 20 በመቶ የሚሆነውን ሕዝቧን ለመከተብ በቂ ነው ብላለች።

የዓለም ባንክ የኬንያ የሕዝብ ብዛት ከ52 ሚሊየን በላይ እንደሆነ ያስቀምጣል።

ክትባቱን በቅድሚያ ከሚወስዱ ሰዎች ዝርዝር ውስጥም ግንባር ቀደም የጤና ባለሙያዎች፣ አረጋውያን እና ከባድ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ጋቪ፤ እያንዳንዱ የኮቪድ-19 ክትባት 3 ዶላር ድረስ እንደሚያስወጣ መናገሩ ይታወሳል።

ጋቪ ወደ ዘጠኝ ከሚጠጉ እጩ ክትባትን ከሚያመርቱ ተቋማት ጋር ስምምነቶችን ተፈራርሟል።

እስካሁን በተደረጉ ምርምሮችና ሙከራዎች በርካታ ተስፋ ሰጪ የክትባት ውጤቶች መገኘታቸው ከመነገሩ ባሻገር፤ በሽታውን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ጥቂት ክትባቶችም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው ለተባሉ ሰዎች በአንዳንድ አገራት መሰጠት ተጀምሯል።

በዚህ ረገድ ቀዳሚውን የተጠቃሚነት ዕድል ያገኙት ባለጸጋ አገራት ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅትም ክትባቶቹ ለሁሉም እንዲዳረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል።

ሌሎች አገራትም ክትባቱን ለማቅረብ ባላቸው አማራጮች ሁሉ እየሞከሩ እንደሆነ እየገለፁ ነው።

ኢትዮጵያም ኮቫክስ ከተሰኘው ዓለም አቀፍ የክትባት ድጋፍ ሰጪና እቅራቢ በኩል ለአገልግሎት ከሚቀርቡት የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ጥያቄ እንዳቀረበች የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባለፈው ሳምንት ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ ጨምረውም ለአገልግሎት ብቁ ከሆኑ የክትባት ዓይነቶች መካከል ኢትዮጵያም እንድታገኝ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፤ በኮቫክስ በኩል ክትባቱን በፍጥነት ለማግኘትና በቅድሚያ መከተብ ለሚገባቸው ወገኖች እንዲደርስ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።

በአፍሪካ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በበሽታው ሲያዙ ከ56 ሺህ በላይ ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ በኢትዮጵያ ከ117 ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል።

ከ72 ሚሊዮን በላይ የምድራችን ነዋሪዎችም በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከ1.6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ ሰበብ ሕይወታቸውን ማጣታቸው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያሳያል።