"ባለቤቴ በኢራን የሞት ቅጣት እየጠበቀ ነው" የሳይንቲስቱ ባለቤት

የፎቶው ባለመብት, CENTER FOR HUMAN RIGHTS IN IRAN
ለዶክተር አህማድሬዛ ጃላሊ ከሌላው ጊዜ የተለየ አልነበረም፤ ያው የተለመደው የሥራ ጉዞ።
በታቀደውም መሰረት ሁለት ሳምንት በኢራኗ መዲና ቴህራን ቆይቶ ወደ መኖሪያው ስዊድን መመለስ ነበር። ነገር ግን ሳይመለስ አሁን አራት ዓመት ተቆጠረ።
እንደወጣም ቀረ፤ በኢራን ለእስር መዳረግ ብቻ ሳይሆን የሞት ፍርድም ተፈርዶበታል።
የመጨረሻ ስንብት ባለማድረጓ ባለቤቱ ቪዳ ሜህራን ኒያ፤ ፀፀቱ የእግር እሳት ሆኖባታል።
የተፈጥሮ አደጋና፣ ድንገተኛ ህመሞች መድኃኒት ባለሙያና ተመራማሪ የሆነው ዶክተር አህማድሬዛ ጃላሊ በየጊዜው ኢራን እየተመላለሰ ጉባኤዎችንና ትምህርቶችንም ይሰጥ ነበር።
ከአራት አመት በፊት ባለቤቱን ከሁለት ሳምንት በኋላ እንገናኛለን ብሎ ነበር ለተለመደ ሙያዊ ተግባሩ ወደ ኢራን ያቀናው።
እዚያ እንደደረሰም በስልክ አውርተዋል።
"ሁለት ሳምንትም ቢሆን መለያየት ቀላል አይደለም" ትላለች ባለቤቱ ቪዳ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ።
ልጇ አባቱ በኢራን እስረኛ እንደሆነ ስለማያውቅ በተቻለ መጠን ያንን ጉዳይ የሚመለከት ነገር እሱ ፊት አታነሳም። አባቱ አሁንም ለሥራ እንደሄደ ነው የሚያስበው።
የስዊድና የኢራን ጥምር ዜግነት ያለው ዶክተር አህማድሬዛ ጃላሊ በኢራን የደኅንነት ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ የሞት ፍርድ ከተፈረደበት አራት ዓመታትን አስቆጥሯል።
የኢራን ባለስልጣናት እንደሚሉት ዶክተሩ መረጃዎችን ለእስራኤሉ የደኅንነት ተቋም ሞሳድ በመስጠት ኢራናዊውን የኒውክሊየር ሳይንቲስቶች ለማስገደል ረድቷል በማለትም ተጠያቂ አድርገውታል።
ጠበቃው በበኩሉ ደንበኛቸው በከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ጥፋተኝነቱን እንዲናዘዝ አድርገውታል ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Vida Mehran-nia
ዶ/ር አህማድሬዛ ብቻውን ወደሚታሰርበት ኢቫን በሚባለው እስር ቤት እንዲዛወር የተደረገ ሲሆን፤ በእስር ቤቱ 209 ተብሎ የሚጠራው አካባቢ እሱን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ ታሳሪዎች ለብቻቸው ተነጥለው በእስር ላይ ይገኛሉ።
በቅርቡ አጠር ላለ ጊዜ በስልክ ከቤተሰቡ ጋር በተነጋገረበት ወቅት የሞት ቅጣት እንደተፈረደበት የነገራቸው ሲሆን፤ ፍርዱም ተፈፃሚ እስኪሆን ድረስ ጥበቃ ላይ ነኝ አለ።
ቪዳ የ45 ዓመት ባለቤቷን የኢራን ባለስልጣናት ሊገድሉትም መሆኑንም ለዓለም አሳውቃለች።
"በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ውስት ሆኖ ነው የሞት ቅጣቱ እንዲቀርለትና ህይወቱንም ለማዳን የምችለውን ነገር ሁሉ እንዳደርግ የጠየቀኝ" በማለት ለቢቢሲ ተናግራለች።
"በአንዲት ጠባብ እስር ቤት ታፍኖ ምንም ነገር የማድረግም ኃይል እንደሌለውም ነው የተሰማው።"
በመቀጠልም የ18 ዓመት ሴት ልጁን አዋራት።
"ድምፁን ከሰማች በኋላ እያለቀሰች ለፖለቲከኞች እንዲሁም ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በመደወል የአባቴን ህይወት አድኑ እያለች መማመፀን ጀመረች" ትላለች ባለቤቱ ቪዳ።
"ቤተሰቡ ሁሉ በጭንቀት ላይ ነው ያለው። ስቃይ ላይ ነን። እንዴት እየሆንን እንደሆነ ማንም ሊረዳው አይችልም።"

የፎቶው ባለመብት, Vida Mehran-nia
ለቤተሰቡ ሸክሙ ከብዶባቸዋል።
"ትንሹ ልጄ አባቱ ወደ ኢራን ሲሄድ የአራት ዓመት ልጅ ነበር። አሁን ስምንት ዓመቱ ነው" ትላለች ቪዳ።
"ስለ አባቱ ሁልጊዜም በየቀኑ ነው የሚጠይቀው፤ አባቱ እሽኮኮ ሲለውና ሲጫወቱ የነበረውንም ጊዜ ያስታውሳል።"
ዶክተር አህማድሬዛ ወደ ስዊድን የሄደው ለትምህርት ሲሆን ወቅቱም በጎሮጎሳውያኑ 2009 ነው።
በስዊድን፣ የስቶክሆልም ካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት የዶክትሬት ትምህርቱንም ለመማር ነበር። ከዓመት በኋላም ቤተሰቡን ወደ ስዊድን ወሰደ።
ከዚያም ወደ ጣልያንም ሄዶ የድህረ- ዶክትሬት ዲግሪውን አገኘ፤ አጠቃላይ ቤተሰቡም ወደ ስዊድን በ2015 ተመለሱ።

ያችን የመጨረሻዋን መጥፎ ጉዞ ወደ ኢራን ከማድረጉ በፊት ቤተሰቡ ቀለል ያለ ኑሮ ነበር የሚኖረው።
ስዊድን ለዶክተር አህማድሬዛ በ2018፣ በአስር ላይ ባለበት ወቅት ነው ዜግነት የሰጠችው።
ይህንንም ተከትሎ አንዳንዶች ዶክተሩ የምዕራቡ ቁልፍ ሰው መሆኑን ማሳያ ነው በማለትም አስተያየታቸውን የሰጡም ነበሩ።
ባለቤቱ ይህንን አስተያየት አትቀበለውም። ዶክተር አህማድሬዛ የዶክትሬት ትምህርቱን ካጠናቀቀበት እለት ጀምሮ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ እንዳላቸውም ትናገራለች።
ዶክተር አህማድሬዛ በስዊድን የተከበረ ሳይንቲስት ነው። ሆስፒታሎችም ሆነ የተለያዩ ግዛቶች አደጋን የሚከላሉበትን መንገድ በተመለከተም ጥልቅ ምርምር ሰርቷል።
ሶደርስጁክሁሴት ሆስፒታል ውስጥም ፎቶው እንዲሁም 'Preparedness and Safe Hospitals: Medical Response to Disasters' የሚለው የዶክትሬት መመረቂያ ሥራው በትልቁ ተሰቅሏል።
ዶክትሬቱንም ሲሰራ ተቆጣጣሪው የነበሩት ፕሮፌሰር ሊዛ ኩርላንድም ጋር ከምርምር ጋር በተያያዘ ለመገናኘት ቀጠሮ ቢይዙም። በኢራን እስር ቤት የተቆለፈበት ዶክተር በቀጠሯቸው ወቅት ሊገኝ አልቻለም።

"በቀጠሯችን መሰረት አለመገኘቱ በጭራሽ ከእሱ የሚጠበቅ ነገር አይደለም። እናም ምን ተፈጥሮ ይሁን እያልኩም ማሰብ ጀመርኩ" ይላሉ ፕሮፌሰር ሊዛ ኩርላንድ።
"ብዙ ጊዜም ወደ ኢራን በሚመላለስበትም ወቅት ምንም ችግር የለም ወይ ደኅንነት ይሰማሃል ወይ? እለው ነበር"
ዶክተር አህማድሬዛ እንደታሰረ ቤተሰቡ ለጓደኞቻቸውና ለምርምር የሥራ አጋሮቹ የመኪና አደጋ እንደደረሰበትና ሆስፒታልም ህክምና እያደረገም እንደሆነ ነበር የተናገሩት።
የእስሩንም ሁኔታ ባለመናገራቸው ነገሮችን ያቀልለታል፤ ቶሎም ይፈታል ብለው አስበው ነበር። ግን የታሰበው አልሆነም። የሞት ፍርድ ተፈረደበት፣ ከዚያም በኋላ ነው ለህዝብ ይፋ ለማድረግ የወሰኑት።
ፕሮፌሰር ሊዛ የሞት ቅጣት እንደተፈረደበት ሲሰሙ በከፍተኛ ሁኔታ ነው የደነገጡት።
"ልዩነት ለማምጣትና የተሻለች ዓለም ለመፍጠርም ከፍተኛ የሆነ ጉጉት ነበረው፤ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ኢራናውያንን ለመርዳት ከፍተኛ እቅድ ነበረው" ይላሉ።
ከዶክተር አህማድሬዛ ጋር በካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት አብረውት የሚሰሩት ፕሮፌሰሮቹ ካታሪና ቦህምና ቬሮኒካ ሊንድስትሮም "በጣም ትሁት፣ ቀናና ጨዋ" ነበር ይሉታል።
ስለ ኢራን አውርቶ አይጠግብም ይላሉ የሥራ ባልደረቦቹ፤ ያለው የፖለቲካ ሁኔታም ሳይበግረው በኢራን ዩኒቨርስቲዎች የማስተማር እቅድ ነበረው።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ከሦስት ዓመት በፊትም 75 የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች ዶክተር አህማድሬዛ እንዲፈታ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢራን ባለስልጣናት ፅፈው ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት እንዲሁ 150 የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች የኢራን ታላቁ መሪ አሊ ሃሜኒ ጣልቃ ገብተው ዶክተሩን እንዲያስፈቱት የሚጠይቅ ደብዳቤ ፅፈዋል።
ባለፈው ወርም የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራው አምነስቲ ኢራን የሞት ቅጣቱን ተግባራዊ እንዳታደርግ ጠይቋል። የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ለኢራን አቻቸው የሞት ቅጣቱ ተፈፃሚ እንዳይሆንም ጠይቀዋል።
ነገር ግን ኢራን የስዊድንን ጥያቄ ተቀባይነት የለውም በማለት "ማንኛውንም ጣልቃ ገብነትን" በተመለከተ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።
የውጭ አገር እንዲሁም ጥምር ዜግነት ያላቸውና በኢራን ሰላይ ናቸው ተብለው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እነዚህን እስረኞች ከውጭ አገር መንግሥታት የሆነ ነገር ለማግኘት መያዣ አድርጋቸዋለች ይላሉ።
ባለፈው ወር ኢራን ለአስር ዓመት በስለላ ወንጀል አስራው የነበረውን እንግሊዛዊ-አውስትራሊያዊ መምህር በሦስት ኢራናዊ እስረኞች ልውውጥ ፈትታዋለች።
ዶክተር አህማድሬዛ የዶክትሬት መመረቂያ የምርምር ፅሁፉን ማስታወሻነቱ ለኢራን ሕዝብ ነው በማለት በመጀመሪያው ገፅ ላይ ያሰፈረውም "በአደጋዎች ህይወታቸውን ላጡ እንዲሁም ህይወታቸውን ላመሰቃቀለው የአለማችን ሕዝቦች፤ በተለይም ለኢራን እንዲሁም ለባም ከተማ ሕዝብ ነዋሪዎች ይሁንልኝ" ይላል።
በጎሮጎሳውያኑ 2003 በኢራኗ ባም ከተማ በደረሰ ርዕደ መሬት 26 ሺህ 271 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
በድንገተኛ ህክምና ላይ የሚያደርገው ምርምር መቼም ቢሆን ለሞት ቅጣት ያበቃኛል ብሎም በህልሙም አስቦ አያውቅም።
ባለቤቱ እንደምትለው ከሁሉ ቅድሚያ ይሰጠው የነበረው ነገር ሰዎችን መርዳት እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከል እንዴት ይቻላል የሚለው ላይ ትኩረት አድርጎ ነበር።
የዶክተር አህማድሬዛ ልጅ በአባቷ እግር ተከትላ አባቷ ዶክትሬቱን የተማረበት ትምህርት ቤት ገብታለች።
የልጇ እዚህ ትምህርት ቤት መግባቷ ለቪዳ ትልቅ ድል ነው፤ በዚህ ጭንቀት ተወጥራ ባለችበትም ወቅት ያለባለቤቷ ድጋፍ ልጇ እዚህ ቦታ ላይ እንድትደርስም ከፍተኛ ሚናን ተጫውታለች።
"የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በከፍተኛ ደረጃ ስታጠናቅቅ ደስታዋን ለመጋራት አባቷ ከጎኗ አልነበረም" ትላለች ቪዳ እያነባች።
"በካሮሊንስካ ኢንስቲትዩት ተቀባይነት ስታገኝም ልክ እንደ አባቷ ህክምናን መረጠች ግን አባቷ አሁን ከጎኗ የለም።"












