ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢራኑ ሳይንቲስት የተገደሉት በሰው አልባ መሣሪያ ነው ሲል መንግሥት አሳወቀ
የኢራኑ ሳይንቲስት የተገደሉት በሰው ሰራሽ ልህቀት [አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ] በታገዘ የጦር መሣሪያ ነው ሲሉ የአብዮታዊ ጠባቂው ምክትል መሪ አስታወቁ።
ሞህሰን ፋክሪዛሄድ ባለፈው ወር መጨረሻ ከቴህራን ከተማ ወጣ ብሎ ነበር የተገደሉት።
እሁድ ዕለት ብርጋዲዬር ጄኔራል አሊ ፋዳቪ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት አንድ ክፍት መኪና ላይ የተተከለ የጦር መሣሪያ ነው።
የጦር መሣሪያው በርካታ ጊዜ ወደ ፋክሪዛሄድ መኪና ቢተኩስም ባለቤታቸው ግን አልተመቱም ብለዋል ጄኔራሉ።
ኢራን ከጥቃቱ ጀርባ እስራኤልና ከሃገር ውጭ የሚንቀሳቀስ ተቃዋሚ ፓርቲ ይገኛሉ ስትል ትወቅሳለች።
እስራኤል በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።
ሳይንቲስቱ እንዴት ተገደሉ?
የኢራን መንግሥት ግድያውን በተመለከተ የሚጋጩ ዘገባዎች አውጥቷል።
ሳይንቲስቱ በተገደሉ ቀን የኢራን መከላከያ ሚኒስቴር የፋክሪዛሄድ ጠባቂዎችና ታጣቂዎች የተኩስ ልውውጥ አድርገዋል ሲል ገልፆ ነበር። አንድ ኒሳን ክፍት መኪና በቦታው ፈንድታ ነበር ይላል በወቅቱ የወጣው መግለጫ።
ሌላኛው ዘገባ በወቅቱ በግድያው ስፍራ የነበሩ አራት የሚሆኑ ታጣቂዎች ተገድለዋል ይል ነበር።
በሳይንቲስቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ደግሞ የኢራን ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊ ግድያው የተፈፀመው ማንም ሰው በሌለበትና ኤሌትሮኒክ በሆነ መንገድ ነው ብለው ነበር።
የአብዮታዊ ጠባቂው ምክትል አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ፋዳቪ ዕሁድ ዕለት በሰጡት መግለጫ ኒሳን መኪና ላይ የተጫነ የጦር መሣሪያ ሳይንቲስቱ ላይ ካነጣጠረ በኋላ ነው የገደላቸው ብለዋል።
ሳይንቲስቱ 13 ጥይቶች እንደተተኮሰባቸው መግለጫው ያትታል።
በሳተላይት የታገዘ ነው የተባለው የጦር መሣሪያ ከሳይንቲስቱ መኪና 10 ኢንች ርቆ የቆመ ነበር ቢባልም ባለቤታቸው ግን አልተገደሉም።
የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒ የሳይንቲስቱን ግድያ እንደሚበቀሉ አሳውቀዋል። ለገዳዮች ፍፁም መራር የሆነ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
ሞህሰን ፋክሪዛሄድ የኢራንን የኒውክሌር ማቀናበሪያ በበላይነት በመምራት ይታወቃሉ።