ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮረናቫይረስ፡ የትራምፕ ጠበቃ በኮቪድ-19 ተይዘው ሆስፒታል ገቡ
የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የግል ጠበቃና የቀድሞው የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ሩዲ ጁሊያኒ በኮቪድ-19 ከተያዙ በኋላ ወደ ሆስፒታል መግባታቸው ተገለጸ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የጠበቃቸውን ሆስፒታል መግባት በማስመልከት ጠበቃው ቶሎ እንዲሻላቸው ምኞታቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸዋል።
ጠበቃው ጁሊያኒ ከምርጫው በኋላ የትራምፕን የፍርድ ቤት ክርክር ሲመሩ የቆዩ ናቸው።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን የ76 ዓመቱ ጠበቃ ሕመም ጸንቶባቸው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ሜድስታር ጆርጅታዎን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እንዲገቡ መደረጉን በስፋት ዘግበዋል።
የቀድሞ የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ የአሁኑ የፕሬዝዳንቱ ጠበቃ መልካም ምኞት የገለጹላቸውን አመስግነው ከሕመማቸው እያገገሙ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዋይት ሐውስ የሚሰራው የጠበቃው ልጅ አንድረው ጁሊያኒ ወላጅ አባቱ እረፍት እያደረጉ እና እየተሻላቸው መሆኑን ገልጿል። ጠበቃው ጁሊያኒ የትኞቹን የበሽታው ምልክቶች እያሳዩ እንደሆነ አልተገለጸም።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አሃዝ ከሆነ በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 14.6 ሚሊዮን የተቃረበ ሲሆን ከ281 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሕመሞች ሕይወታቸው አልፏል። ይህም በዓለማችን ከፍተኛው ነው።
ጠበቃው የምርጫውን ውጤት ለማስቀየር ወደ በርካታ ግዛቶች ተዘዋውረዋል። በጉዟቸው ወቅትም ጁሊያኒ የኮሮናቫይረስ ክልከላዎችን ሲተላለፉ ታይተዋል ተብሏል። የአፍ እና አፈንጫ መሸፋኛ ሳይደርጉ እና ርቀታቸውን ሳይጠበቁ ጁሊያኒ ተስተውለዋል።
ባሳለፍነው ሐሙስ ጆርጂያ ግዛት የነበሩት ጁሊያኒ፤ ምንም አይነት ማስረጃ ሳያቀርቡ በጆርጂያ የተካሄደው ምርጫ ተጭበርብሯል ሲሉ ከሰው ነበር። ጠበቃውን ጨምሮ በርካታ የትራምፕ የቅርብ አማካሪዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ቦሪስ ኢፕስታይን እና ኬይሊ ማኬንሊ በቅርቡ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ የፕሬዝዳንት ትራምፕ የቅርብ አማካሪዎች ናቸው።