ኢራን ከተፈቀደላት በላይ ዩራኒየም ማብላላት ልትጀምር ነው

ኢራን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሰላማዊ ተግባር ነው የምትለውን የኒኩሊየር ግንባታ ማዕከሎችን የሚመረምረውን ቡድንን ላለመቀበል ወስናለች።

ይህ ብቻም ሳይሆን ዩራኒየም ማበልጸግ የምትችልበትን ጣሪያ አልፋ ለመሄድ እንደራሴዎቿ ወስነዋል።

ኢራን ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ የምታደርገው በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቅብ በ2 ወራት ውስጥ ካልተነሳላት ነው።

ኢራን ዩራኒየም እንድታበለጽግ የተፈቀደላት ምጣኔ 3.67 በመቶ ብቻ ሲሆን አሁን ወደ 20 በመቶ ለማሳደግ ነው የወሰነችው።

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሩሐኒ ይህንን የምክር ቤቱን ውሳኔ እንደተቃወሙት ተናግረዋል።

ይህ የሸንጎው ያልተጠበቀ ውሳኔ የመጣው የጎምቱው የኒኩሊየር ሳይንቲስቷን የሞሐሰን ፋክሪዘድን ግድያ ተከትሎ ነው።

ሳይንቲስቱ ሞሐሰን የተገደሉት ባለፈው ሳምንት ሲሆን ከቴህራን ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ ከርቀት መቆጣጠርያ በተበጀለት ፍንዳታ መገደላቸውን የኢራን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ኢራን ሳይንቲስቷን የገደለችባት እስራኤል እንደሆነች ታምናለች።

እስራኤል ስለ ግድያው ለጊዜው ያለችው ነገር የለም።

ጎምቱው ሳይንቲስት ሞሐሰን በኒኩሊየር ግንባታው የመሪነት ሚና የነበራቸው ሳይንቲስት እንደሆኑ ይነገራል።

የኢራን መንግሥት ይህ የኒኩሊየር ግንባታ ለሰላማዊ ተግባር የሚውል ነው ይላል።

የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ናታንያሁ ከዚህ ቀደም በኢራን ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ የኚህን ሟቹን ሳይንቲስት ስም አንስተው ነበር።

ኢራን ከአምስቱ ኃያላን ጋር በ2015 ከተስማማችበት መጠን በላይ ዩራኒየም አብላላለሁ ወደሚለው ውሳኔ የደረሰችው አሜሪካ ከዚህ ስምምነት ወጥታ በጫነችባት ከባድ ማእቀብ የተነሳ ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቷ ነው።

በዚህ አዲስ በጸደቀው ሕግ ቴህራን ለአውሮጳ የስምምነቱ ፈራሚ አገራት 2 ወራት የማስጠንቀቂያ ጊዜን ትሰጣለች።

በዚህ ጊዜ ውስጥ ፈራሚዎቹ የአውሮጳ አገራት አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን ማእቀብ ሊያላላ የሚችል ሁኔታን መፍጠር ካልቻሉ ሁለት እርምጃዎችን ትወስዳለች።

አንዱ ዩራኒየም ለማብላላት የተፈቀደላትን መጠን አልፎ መሄድ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የተባበሩት መንግሥታትን የኑክሊየር ተቆጣጣሪ ቡድን በናታናዝና ፎርዶው የኒኩሊየር መብሊያ ጣቢያ ጉብኝትና ቁጥጥር እንዳያደርግ ማገድ ነው።

የኢራን ፋርስ ዜና አገልግሎት ይህ የሸንጎው ውሳኔ ፕሬዝዳንቱ እንዲያስፈጽሙ በደብዳቤ በይፋ እንደጠየቀ ዘግቧል።

ሮሐኒ የሸንጎውን ውሳኔ የዲፕሎማሲ ቀውስ የሚፈጥር ነው ሲሉ ያላቸውን ልዩነት አስቀምጠዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ከአምስትዮሹ የ2015 የኑኩሊየር ስምምነት የወጡት በግንቦት 2018 ነበር። ከዚህ በኋላ የኢራንን ምጣኔ ሀብት ክፉኛ የሚጎዳ በፋይናንስ ተቋማትና በነዳጅ ሽያጭ ላይ ያተኮረ ከባድ ማዕቀብ ጥለውባታል።

አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ሰላም ስምምነቱ ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል። ይህንንም በይፋ ተናግረዋል።