ቻይና ሰንደቅ ዓላማዋን ጨረቃ ላይ ተከለች

ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማዋን ጨረቃ ላይ ተከለች። ይህ የሆነው ተቀናቃኟ አሜሪካ ሰንደቅ አላማዋን ጨረቃ ላይ ካስቀመጠች ከ50 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው።

ከቻይና ብሔራዊ የህዋ አስተዳደር ተቋም ይፋ የተደረጉት ምስሎች ባለአምስት ኮከቡ ቀዩ የቻይና ሰንደቅ ዓላማ ነፋስ በሌለበት የጨረቃ ገጽ ላይ ተተክሎ ያሳያሉ።

ምስሎቹ የተነሱት ቻንጌ-5 የተባለው የህዋ አሳሽ መንኮራኩር ሐሙስ ዕለት ከጨረቃ ላይ የአለት ናሙናዎችን ሰብስቦ ከመመለሱ በፊት እንደሆነ ተነግሯል።

በቻይና መንግሥት የሚዘጋጀው 'ግሎባል ታይምስ' ጋዜጣ እንዳለው፤ የቻይና ሰንደቅ ዓላማ በጨረቃ ላይ መተከሉ የአሜሪካው አፖሎ 11 ጉዞ ወቅት የተፈጠረው አይነት "ደስታንና መነቃቃትን" ፈጥሯል።

በጨረቃ ገጽ ላይ የተተከለው የቻይና ሰንደቅ ዓላማ 2 ሜትር ስፋትና 90 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ክብደቱም አንድ ኪሎ ያህል እንደሆነ ተነግሯል።

"በምድር ላይ የምንጠቀመው አይነት ማንኛውም የሰንደቅ ዓላማ ጨርቅ በጨረቃ ላይ ያለውን ሁኔታ መቋቋም አይችሉም" ያሉት የጨረቃው ጉዞ ፕሮጀክት መሪ ሊ ዮንፌንግ ለግሎባል ታይምስ ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ሰንደቅ ዓላማው የተለያዩ የአየር ሁኔታዎችን እንዲቋቋም ተደርጎ ነው የተሰራው።

የቻይና ሰንደቅ ዓላማ በጨረቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ቀደም ሲል ወደ ጨረቃ በተጓዙት ቻንጌ-3 እና ቻንጌ-4 የተባሉት የአሰሳ መንኮራኩሮች ላይ በተሳሉት ባንዲራዎች አማካይነት ሲሆን፤ ከጨርቅ ተሰርቶ የጨረቃ ገጽ በሰንደቅ ላይ የተተከለው ግን የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

የቻይናን ሰንደቅ ዓላማ በመትከል የመጀመሪያው የሆነው ቻንጌ-5 የተባለው የህዋ ተልዕኮ ባለፉት ሰባት ዓመታት ቻይናን በተሳካ ሁኔታ ጨረቃ ላይ እንድታርፍ ካደረጉት ሦስተኛው ነው።

ከዚህ በፊት በተደረጉት የቻይና ሁለት የጨረቃ ጉዞዎች ወቅት መንኮራኩሮቹ ላይ በቀለም ከተሳለው የቻይና ባንዲራ ውጪ በጨረቃ ገጽ ላይ የአገሪቱ ሰንደቅ አልተተከለም ነበር።

አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በጨረቃ ገጽ ላይ ሰንደቅ ዓላማዋን የተከለችው ከ50 ዓመታት በፊት እአአ በ1969 አፖሎ 11 የተባለችው መንኮራኩር ወደ ጨረቃ ባደረገችው ጉዞ ነበር። ከዚያ በኋላም እስከ 1972 (እአአ) በተደረጉ ጉዞዎች አምስት ጊዜ ሰንደቅ ዓላማዋን ጨረቃ ላይ ተክላለች።

ከስምንት ዓመት በፊት በናሳ ሳተላይቶች የተነሱ ፎቶዎች እንዳሳዩት በጨረቃ ላይ ተተክለው ለዓመታት የቆዩት አምስቱም የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማዎች በቦታቸው ላይ የሚታዩ ቢሆንም በፀሐይ ብርሃን ምክንያት ደብዝዘው ወደ ነጭነት መቀየራቸውን ባለሙያዎች ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የመጀመሪያውን የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ጨረቃ ላይ የተከለው ጠፈረተኛ በዝ አልድሪን ሲሆን፤ ከመንኮራኩሯ ግርጌ ተክሎት ነበረ። ምናልባትም መንኮራኩሯ ወደ ምድር ለመመለስ ስትነሳ በሚፈጠረው ከባድ ግፊት ከተተከለበት ቦታ ተነቅሎ ሳይወድቅ አይቀርም ብሎ ነበር።