ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትግራይ ፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ገለጸ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል የሚገኙ በርካታ ከተሞችን እየተቆጣጠረ ወደ መቀለ እየቀረበ መሆኑን አስታወቀ።
ሠራዊቱ በትግራይ ክልል በሚገኙና በህወሓት በሚመሩት ኃይሎች ላይ ዘመቻ ከከፈተ ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ኢላማውን መቀለ ላይ ማድረጉ ተነግሯል።
የፌደራል ሠራዊቱ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም እንደተናገሩት መንግሥት የመጨረሻ ምዕራፍ ያለው ዘመቻ ከተጀመረ በኋላ በመቀለ አቅራቢያ የሚገኙት ሃውዜን፣ አል ነጃሺ፣ አዲቀየህ፣ ማይመሳኖን፣ ውቅሮና ሌሎች አካባቢዎችን መቆጣጠር እንደቻሉ ገልጸዋል።
እነዚህ አካባቢዎች በአገሪቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር እንደገቡ የተነገረው የህወሓት አመራሮችና የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት እጃቸውን እንዲሰጡ የተቀመጠው የሦስት ቀናት ገደብ ማብቃቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሐሙስ ዕለት ሠራዊቱ ዘመቻውን እንዲጀምር ካዘዙ በኋላ ነው።
ሌተናል ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት ሠራዊቱ በአድዋ፣ በአዲግራትና በራያ በኩል ባሉ የተለያዩ ግንባሮች ከሐመስ ጀምሮ ባካሄደው ዘመቻ በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠሩን አመልክተው፤ መቀለ አቅራቢያ ያለውን መሰቦ ተራራን በመያዝ ወደ ከተማዋ እንደሚያመሩ ገልጸዋል።
ወታደራዊ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ሦስት ሳምንት ያለፈው ሲሆን የኢትዮጵያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎችን በመቆጣጠር በማዕከላዊ ምሥራቅ የክልሉ ክፍል ውስጥ የምትገኘውን ዋና ከተማዋ መቀለን ለመያዝ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ወታደራዊ ባለስልጣኑ አመልክተዋል።
በትግራይ ክልል የሚገኙት የስልክ፣ የሞባይል እና የኢንተርኔት ግንኙነቶች በመቋረጣቸው ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት ከባድ ቢሆንም፤ የተለያዩ ተቋማት እንደሚሉት ከሆነ በግጭቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀረ የተገመተ ሲሆን በአስር ሺዎች ደግሞ ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት ሱዳን ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አርብ ዕለት ከአፍሪካ የሰላም መልዕክተኞች ጋር ባደረጉት ውይይት በአካባቢው ያሉ ሰላማዊ ሰዎች እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።
እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት አብቅቶ በውይይት ወደ መቋጫ እንዲያገኝ ማድረግን በተመለከተ የተባለ ነገር የለም። የኢትዮጵያ መግግሥት ግን ከህወሓት አመራሮች ጋር ምንም አይነት ውይይት እንደማይኖር በተደጋጋሚ አስታውቋል።
ወታደራዊ ዘመቻው ወደ መቀለ እተቃረበ ባለበት በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ነዋሪዎች እንዳይጎዱ የተለያዩ አካላት ማሳሰባቸውን ተከትሎ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ 500 ሺህ በላይ ሰዎች በሚኖሩባት መቀለ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሠራዊቱ አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ገልጸ እንደነበር ይታወሳል።
መቀለን የሚቆጣጠረው የህወሓት ኃይል አመራሮች እጃቸውን እንደማይሰጡና ከመንግሥት በኩል የሚመጣውን ጥቃት እንደሚጋፈጡ ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመቀለን የሚያጠቃ ከሆነ የጦር ወንጀሎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አስቀምጧል።
በተጨማሪም የሰብዓዊ እርዳታ ለሚፈልጉ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ለማድረስ ምቹ ሁኔታ አለመኖሩንም ድርጅቱን እንዳሳሰበው አመልክቷል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሐሙስ ዕለት እንዳሉት በመንግሥት ቁጥጥር በሚገኙ አካባቢዎች "ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ እንደሚከፈት እና ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ጋር ለመስራት፣ ሰላማዊ ዜጎችንና ድጋፍ የሚፈልጉትን ለመጠበቅ" ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየው አለመግባባት ባለፈው ዓመት ሊካሄድ የነበረው አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ የበለጠ መካረሩ ይታወሳል።
በዚህም ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል የተካሄደው የተናጠል ምርጫን የፌደራል መንግሥቱ ተቀባይነት የሌለውና ሕገ ወጥ በማለት ከክልሉ አስተዳደር ጋር የነበረውን የቀጥታ ግንኙነት አቋርጦ ነበር።
ይህንንመ ተከትሎ ጥቅም 23/2013 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትግራይ ክልል በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ይፋ ካደረጉ በኋላ የፌደራሉ ሠራዊት በትግራይ ክልል ኃይሎች ላእ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ።
ይህ ወታደራዊ ግጭት ሦሰት ሳምንት ያለፈው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊቱት ወደ መቀለ ለመግባት እየተዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል።