ኡጋንዳ ፡ የተቃዋሚው መታሰር በቀሰቀሰው ተቃውሞ 28 ኡጋንዳውያን ሞቱ

ሙዚቀኛና ታዋቂ ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ቦቢ ዋይን መታሠሩን ተከትሎ ኡጋንዳ ውስጥ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። ያለፈው ሳምንት ረቡዕ በጀመረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ቢያንስ 28 ሰዎች ሞተዋል።

የአገሪቱ የደኅንነት ሚንስትር ኤሊ ቱምዋይን፤ የኡጋንዳ ፖሊሶች "የተቃዋሚዎች ነውጥ ከመጠን በሚያልፍበት ጊዜ ተኩሰው የመግደል መብት አላቸው" ብለዋል።

ቦቢ ዋይን የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ኮሮናቫይረስን በማሰራጨት ክስ ተመስርቶበታል። ከዚያም አርብ በዋስ ተፈቷል።

የሰብዓዊ መበት ተሟጋቾች እንደሚሉት ቦቢ ዋይን (ሮበርት ኪያጉላኒ) የታሰረው ከምርጫው በፊት የተቃዋሚዎችን ድምጽ ለማፈን ነው።

የኡጋንዳ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ጥር ላይ ይካሄዳል።

ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን ከሚፎካካሩ 11 እጩዎች መካከል አንዱ ቦቢ ዋይን ነው።

ሙሴቪኒ እአአ በ1986 ነበር ሥልጣን የያዙት።

ቦቢ ሲታሰር ደጋፊዎቹ በመዲናዋ ካምፓላና በሌሎች ሁለት ከተሞች መንገድ በመዝጋትና ጎማ በማቃጠል ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎቹ ላይ አስለቃሽ ጭስና ጥይት ተኩሰዋል።

የደኅንነት ሚንስትሩ እንደሚሉት 11 የጸጥታ ኃይሎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። "ስለዚህም ተቃዋሚዎች ነውጥ ሲያነሱ ፖሊሶች የመተኮስ መብት አላቸው" ብለዋል።

ፖሊስ በተቃውሞው የሞቱት 28 ሰዎች ናቸው ቢልም፤ አሶሺትድ ፕሬስ ዜና ወኪል ግን የፖሊስ አስክሬን ምርመራና የጤና ዘርፍ ኃላፊን ጠቅሶ 37 አስክሬኖች እንደነበሩ ገልጿል።

ሰኔ ላይ ቦቢ ዋይን የምርጫ ቅስቀሳ እንሚያደርግ ተናግሮ ነበር። በወረርሽኙ ሳቢያ ቅስቀሳ አይደረግም የሚል መመሪያ ቢወጣም፤ ተቃዋሚው መመሪያውን እንደሚጥስ ገልጿል።

ሙሴቪኒ "ሕዝቡን ይፈሩታል" ሲልም ተናግሯል።

የኡጋንዳ መንግሥት ቃል አቀባይ ዶን ዋንያማ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ "ባለሥልጣናት እጃቸውን አጣምረው ሥርዓት አልበኛነት ሲስፋፋ አያዩም።"

ሙሴቪኒ በምርጫ ኮሚሽን እና የጤና ሚንስትር የወጣውን መመሪያ መከተላቸውንም ጠቅሰዋል።

ሂውማን ራይትስ ዋች እንደሚለው፤ የኡጋንዳ ባለሥልጣናት የኮቪድ-19 የጥንቃቄ መመሪያዎችን በመጠቀም ተቃዋሚዎችን ለማፈን እየሞከሩ ነው።

ገዢው ፓርቲ ትልልቅ የቅስቀሳ መድረኮች እንዳዘጋጀም የመብት ተሟጋች ቡድኑ አጣቅሷል።

ቦቢ ከታሰረ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር ከጠበቃዎቹ ጋር መገናኘት የቻለው።

ክስ የተመሰረተበት የሕብረተሰብ ጤና መርህን በመጣስ ሲሆን፤ ይህም እስከ 7 ዓመት በእስር ሊያስቀጣ ይችላል።

የፍርድ ቤቱ ሂደት ሲከናወን ከፍተኛ ጥበቃ እየተካሄደ ነበር።

ተቃውሞው ሲቀሰቀስ ፖሊሶች የኃይል እርምጃ መውሰዳቸው ኡጋንዳውያንን አስደንግጧል።

ይህ ክሰተት ቦቢ ዋይን የፕሬዘዳንት እጩ መሆኑ ከተገለጸ ወዲህ የተቀሰቀሰ ከፍተኛ ተቃውሞ ነው።

ተቃውሞውን ተከትሎ የጸጥታ ጥበቃው ተጠናክሯል።

ወደ ካምፓላ የሚወስዱ ጎዳናዎች እንደሚጠበቁና ከምሽቱ 3 ሰዓት የሚጀምር የሰዓት እላፊ ገደብ እንደሚጣል ተገልጿል።

ከሦስት አሰርታት በላይ በሥልጣን የቆዩት ሙሴቪኒ ተቃዋሚዎችን በኃይል በማፈን ይተቻሉ። እሳቸው ግን ክሱን አይቀበሉም።