ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሙዚቀኛው የፓርላማ አባል በኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ላይ በመሳለቁ ተከሰሰ
የኡጋንዳ ፓርላማ አባልና ታዋቂ የፖፕ ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይን በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ላይ በመሳለቅና ፕሬዝዳንቱን በማስቆጣት ክስ ተመሰረተበት።
ይህ አዲስ ክስ በቦቢ ዋይን ላይ ከዚህ በፊት ከቀረበበት ክስ ላይ ተጨማሪ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት በሰሜናዊ ኡጋንዳ በምትገኘው የአሩዋ ከተማ ውስጥ ፕሬዝዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜ የፓርላማ አባሉና አብረውት የነበሩ ደጋፊዎቹ በፕሬዝዳንቱ መኪኖች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል በሚል ተይዞ ነበር።
ሙዚቀኛውና የፓርላማ አባሉ ቦቢ ዋይን በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ እድሜ ልክ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ተነግሯል።
ዋይንና በርካታ ባልደረቦቹ እስር ቤት በቆዩበት ወቅት ማሰቃየት እንደተፈጸመባቸው ቢናገሩም ባለስልጣናት ግን ክሱን ያስተባብላሉ።
ትክክለኛ ስሙ ሮበርት ኪያጉላኒይ የሆነው ቦቢ ዋይን አሁን ከቀረበበት ክስ በተጨማሪ ባለፈው ዓመት በሞባይል ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎትና በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ ግብር በሚጥለውን ሕግ ላይ ተቃሞን በማካሄዱ በሌላ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበታል።
ሙዚቀኛው የፓርላማ አባል ቦቢ ዋይን ለሰላሳ ዓመታት ስልጣን ላይ የቆዩትን የአገሪቱን ፕሬዝዳንት በመቃወም በኩል ዋነኛው ሰው ሲሆን፤ በቅርቡም ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የፕሬዝዳንትናት ምርጫ ላይ በተፎካካሪነት እንደሚቀርብ አሳውቋል።