ኮሮናቫይረስ፡ የፌስቡክ ሳንሱር ሠራተኞች ፌስቡክን ከሰሱ

በቁጥር ከ200 በላይ የሆኑ ፌስቡክ የሚለጠፉ ይዘቶችን የሚከታተሉ የሳንሱር ሠራተኞች ፌስቡክ ላይ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

ቅሬታ ያቀረቡት "የፌስቡክ ኩባንያ በዚህ አደገኛ በሆነው የወረርሽኝ ወቅት "ቢሮ ገብታችሁ ሥሩ እያለ ያስጨንቀናል" በሚል ነው፡፡

ሠራተኞቹ ቢሮ ገብቶ መሥራት ለተህዋሲው ስለሚያጋልጠን እንደተለመደው ከቤታችን ሆነን ልንሠራ ይገባል ይላሉ፡፡

የፌስቡክ ኩባንያ የሚያስጨንቀው ትርፍን ማጋበስ እንጂ የኛ የሳንሱር ሠራተኞቹ ደኅንነት ከመጤፍም አይቆጥረውም ይላሉ፡፡

ሠራተኞቹ ድርጅታቸው ፌስቡክ ለሰራተኞቹ ማሰብ እንዲጀምርና ከቤት ሆኖ መሥራትን እንዲያበራታታ እንዲሁም የወረርሽኝ ጊዜ አበል እንዲያስብላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ፌስቡክ በበኩሉ ከጠቅላላ የሳንሱር ሰራተኞች ወደ ቢሮ ተመለሱ ያልኳቸው በጣም ጥቂቶቹን ነው ሲል ክሱን አስተባብሏል፡፡

በዓለም ላይ ካሉን 15ሺህ የሳንሱር ባለሙያዎች አብዛኛዎቹ ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ አድርገናል ሲል ኩባንያው በቃል አቀባዩ በኩል ተናግሯል፡፡

ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ ፌስቡክ ሰራተኞቹ እስከ 2021 ዓ.ም የበጋ ወር ድረስ ከቤት ሆነው እንዲሰሩ መመርያ አውጥቶ በዚህም ሲወደስ ቆይቶ ነበር፡፡

ፌስቡክ የጥላቻ ንግግን የሚያዛምቱ፣ ሐሳዊ መረጃን የሚረጩ፣ ሕጻናትን ከወሲባዊ ምሥል ጋር የሚያስተሳስሩ፣ አሉባልታን የሚነዙ ይዘቶችን ቆርጠው የሚጥሉለት የሳንሱር ባለሙያዎችን በመላው ዓለም ቀጥሮ ያሰራል፡፡

ይህንን የሳንሱር ሥራ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ለመተካት ፌስቡክ ብዙ ጥረት አድርጎ ነገር ግን አልተሳካለትም፡፡

የጥላቻ ንግግርንና ሌሎች ፌስቡክ በገጹ እንዲስተናገዱ የማይፈልጋቸው ይዘቶችን ለቅሞ ከጨዋታ ውጭ በማድረግ የሳንሱር ሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ለኩባንያው በጻፉት የክስ ጦማር ይህን ብለዋል፡-

"እኛ ተበዳዮች ፌስቡክን ከጥላቻ ንግግር፣ ከሐሳዊ መረጃ ሥርጭት እያጸዳን የማይተካ ሚና ስንጫወት ድርጅቱ ግን ከኛ ጤና ይልቅ ትርፍ አስጨንቆት ወደ ቢሮ ተመለሱ ማለቱ ያስተዛዝባል፡፡ ለትርፍ ተስገብግቦ የኛን ጤና ቸል ማለቱ ከፍ ያለ የሞራል ዝቅጠት ነው፡፡"

የፌስቡኩ አለቃ ማርክ ዙከርበርግ ያልተገቡ የፌስቡክ ይዘቶች በሰው ሰራሽ ልህቀት (አርተፊሻል ኢንተለጀንስ) መተካት አለባቸው እንጂ በሳንሱር ሰራተኞች በባህላዊ መንገድ መሰራት የለባቸውም ብሎ ያምናል፡፡

ሆኖም አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ሁሉም የፌስቡክ ይዘቶች ብቻውን መልቀም ተስኖታል፡፡ የሳንሱር አድራጊዎች ጣልቃ ገብነት ያስፈለገውም ለዚሁ ነው፡፡